ቀጥታ፡

ኮርፖሬሽኑ በተኪ ምርትና በውጭ ምንዛሬ ግኝት ላይ የጀመረው እንቅስቃሴ ለዘርፉ እመርታዊ ለውጥ ወሳኝ ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 4/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን በተኪ ምርትና በውጭ ምንዛሬ ግኝት ላይ የጀመረው እንቅስቃሴ ለዘርፉ እመርታዊ ለውጥ ወሳኝ ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ዛሬ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን የቃሊቲ ኢንዱስትሪ ዞን እና የልህቀት ማዕከልን ጎብኝተናል ብለዋል።


 

ኮርፖሬሽኑ በተለያዩ ሀገራዊ ስትራቴጂክና ግዙፍ ፕሮጀክቶች ላይ በመሳተፍ እያበረከተ ያለውን አስተዋጽዖ ለማጠናከር የጀመረው ተቋማዊ ሪፎርም አበረታች ነው ሲሉም ገልጸዋል።

ከዚህም ባለፈ የኮንስትራክሽን ግብዓት ማምረቻ ኢንዱስትሪ ዞን በመገንባት በተኪ ምርትና በውጭ ምንዛሬ ግኝት ላይ የጀመረው እንቅስቃሴ ለዘርፉ እመርታዊ ለውጥ ወሳኝ ነው ብለዋል።

የኢንዱስትሪ ዞኑ የማምረት ዐቅሙን በማሳደግ የግንባታ ግብአቶችን እያመረተ መሆኑ በዘርፉ የሚያጋጥም የግብአት እጥረትን በእጅጉ ይቀርፋል ሲሉም አክለዋል።


 

ኮርፖሬሽኑ የኢትዮጵያን የግንባታ ኢንዱስትሪ ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ ለማድረግ ተቋማዊና ሀገራዊ ሚናውን ማጠናከርና ዐቅሙን እንዲያጎለብት መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላልም ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም