በሐረሪ ክልል "በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ" ወደ ምርት የገቡ ኢንዱስትሪዎች ለዜጎች የስራ እድል እየፈጠሩ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሐረሪ ክልል "በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ" ወደ ምርት የገቡ ኢንዱስትሪዎች ለዜጎች የስራ እድል እየፈጠሩ ነው
ሐረር፤ ህዳር 4/2017 (ኢዜአ)፦ በሐረሪ ክልል "በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ" ወደ ምርት የገቡ ኢንዱስትሪዎች ለዜጎች የስራ እድል እየፈጠሩ መሆኑን በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶች ገለጹ።
በንቅናቄው ወደ ምርት ከገቡት አምራቾች መካከል በስፖንጅ ፎም ምርት የተሰማሩት አቶ ሳቢት መሀመድ እንደገለጹት የኢንቨስትመንት ፍቃድ ወስደው ወደ ስራ እንዲገቡ የክልሉ መንግስት ድጋፍና ክትትል ማድረጉን ጠቅሰዋል።
ፋብሪካውም በአሁኑ ወቅት ከ30 በላይ ለሚሆኑ ስራ ፈላጊዎች የስራ እድል መፍጠሩን ጠቁመው ሌሎችም 20 ሰዎች ወደ ስራው ለመቀላቀል ስልጠና እየወሰዱ መሆኑን ተናግረዋል።
መንግስት ባመቻቸላቸው የማምረቻ ቦታ የባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪ እየገጣጠሙ እንደሚገኙና ስራውን በማሻሻል ተሽከርካሪዎችን ወደ ኤሌትሪክ ሲስተም ለመቀየር መዘጋጀታቸውን የነገሩን ደግሞ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የተሰማሩት አቶ መሃመድ ኢብራሂም ናቸው።
የሚገጣጠሙት ተሽከርካሪዎች ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በመተካት የውጪ ምንዛሬን ለማስቀረትና ለዜጎች የስራ እድል የመፍጠር እቅም እንዳላቸው አክለው የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማበልጸግ ጠቀሜታቸው የጎላ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የአዱ ዱቄት ፋብሪካ ስራ አስኪያጅ አቶ ሃብታሙ መኮንን በበኩላቸው ለ65 ዜጎች የስራ እድል መፍጠራቸውን ተናግረዋል።
ቀደም ሲል ከስንዴ ምርት ጋር ተያይዞ ያጋጥም የነበረ የምርት እጥረት በመቀረፉ ምርታማነታቸው ማደጉን አስታውሰው ዘርፉን በማስፋትም በቀጣይ የፓስታና መኮሮኒ ፋብሪካ ለመክፈት እቅድ እንዳላቸው ተናግረዋል።
የሐረሪ ክልል የኢንተርፕራይዞች ልማትና ኢንዱስትሪ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሐምዲ ሰለሃዲን እንደተናገሩት ከኢኮኖሚ ሪፎርም ማሻሻያው በኋላ በክልሉ በኢንዱስትሪው ዘርፍ መነቃቃት ተፈጥሯል።
በተለይ አንዳንድ ኢንዱስትሪዎች ከገንዘብ እጥረትና ከውጪ ምንዛሬ ጋር በተያያዘ ወደ ግንባታና ማምረት ስራ ሳይገቡ መቅረታቸውን አስታውሰው በአሁኑ ወቅት የገንዘብ ብድር በመመቻቸቱ ወደ ስራ እንዲገቡ አስችሏል ብለዋል።
አቶ ሐምዲ አያይዘውም “የኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ በተለይ በግብዓት፣ በሃይል አቅርቦትና በሌሎች ምክንያት ስራ ያቆሙ ኢንዱስትሪዎች ወደ ስራ እንዲገቡ ማስቻሉንም አክለዋል።
በተለይ የኢንዱስትሪው ዘርፍ በክልሉ ለዜጎች ከፍተኛ የስራ እድል እየፈጠረ እንደሚገኝ ጠቁመው የክልሉ መንግስትም ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።