ዓለም አቀፍ ሁነቶችን ለማዘጋጀት ምቹ ሁኔታ እየፈጠሩ ያሉት አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎች - ኢዜአ አማርኛ
ዓለም አቀፍ ሁነቶችን ለማዘጋጀት ምቹ ሁኔታ እየፈጠሩ ያሉት አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎች

በኢትዮጵያ የሚገኙ የተፈጥሮ፣ የታሪክ፣ የባህልና የወግ እሴቶች ለቱሪስት መስህብነት አቅም የሚፈጥሩ ሃብቶች ናቸው።
ቱሪዝም ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ እድገትና በጎ ገጽታዋን ለመገንባት ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው ዘርፍ ነው፡፡
ኢትዮጵያ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ሃብቶች የታደለች ብትሆንም ዘርፉ ለረጅም ዘመናት ተገቢውን ትኩረት ሳያገኝ በመቆየቱ በሚገባው ልክ ጥቅም መስጠት አልቻለም።
ባለፉት ስድስት የለውጥ ዓመታት ለዘርፉ እድገት ማነቆ የሆኑ ተግዳሮቶችን በመፍታት ሀገሪቱ ከዘርፉ የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ ልዩ ትኩረት በመስጠት እየተሰራበት ይገኛል።
ለአብነትም አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎችን የማልማት እና ነባር የቱሪስት መስህቦችን የማደስና የመንከባከብ ስራ ማንሳት ይቻላል።
ከእነዚህ ውስጥ በአዲስ አበባ የተገነቡት አንድነት ፓርክ፣ ወዳጅነት ፓርክ እና አድዋ መታሰቢያ ሙዚየም ተጠቃሽ ናቸው።
ይህም ከተማዋን የቱሪስት መዳረሻና ተመራጭ የቱሪዝም ስፍራ እንድትሆን እያደረጋት ይገኛል።
በአዲስ አበባ የተገነቡት አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎች አለም አቀፍ ሁነቶችን ለማዘጋጀት ምቹ ሁኔታ እየፈጠሩ መሆናቸውን የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ገልጿል።
በቢሮው የቱሪዝም መዳረሻ ልማት እና የሀገር ውስጥ ቱሪዝም ማስፋፋት ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን አይናቸው ለኢዜአ እንደገለጹት በአዲስ አበባ በርካታ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎችን የማልማት ስራ በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡
የከተማዋን ገጽታ ለመገንባትና የቱሪስት መዳረሻነቷን ማሳደግ የሚያስችሉ መሰረተ ልማቶች መገንባታቸውን ገልጸዋል።
በተጨማሪም በከተማዋ ነባር የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎችን የጎብኚዎች ዓይን በሚስብ መልኩ ልዩ ልዩ እሴቶች ተጨምሮባቸው ለአገልግሎት ክፍት የሆኑበት ሁኔታ መኖሩን አስታውቀዋል።
በከተማዋ አዳዲስ የቱሪዝም ስፍራዎች የማልማትና ነባር የቱሪስት መስህቦችን የማደስ ስራ በትኩረት መከናወኑን አስረድተዋል፡፡
ይህም መዲናዋ የተለያዩ አለም አቀፍ ሁነቶችን የምታዘጋጅበትን ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የቱሪስት አስጎብኚ ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዝዳንት ኤንዲ አሰፋ በበኩላቸው በከተማዋ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎችን የማልማት ስራ ትኩረት መሰጠቱ አዲስ አበባ ከሌሎች ትላልቅ ከተሞች ጋር የምትወዳደርበትን አቅም የሚፈጥር መሆኑን ተናግሯል።
ከዚህም ባለፈ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች በለሙ ቁጥር ጎብኚዎች ቦታዎችን ለማየት ፍላጎት የሚያድርባቸው ሲሆን ሀገሪቱ ከዘርፉ የምታገኘው ገቢ እንዲያድግ ያደርጋል ብሏል፡።
በከተማዋ የሚገኙ የቱሪዝም ሀብቶችን በተገቢው ማስተዋወቅ ወሳኝ ጉዳይ በመሆኑ ቢሮው ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀራርቦ እየሰራ እንደሚገኝም አቶ ሳምሶን ገልጸዋል።
አስጎብኚዎች በከተማዋና በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ የቱሪስት ሀብቶችን በሚገባቸው ልክ በማወቅ በተጠናከረ መልኩ ለአለም አቀፍ ጎብኚዎች ማስተዋወቅ እንዳለባቸው የገለጹት ደግሞ አቶ ሳምሶን ናቸው።
የጥምቀት በዓል፣ የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ እና ሌሎች በርካታ ሁነቶችን ከተማዋ የምታስተናግድ በመሆኑ ይህንኑ ለዓለም ሀገራት በስፋት የማስተዋወቅ ስራ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጧል።