ቀጥታ፡

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ለዕዳ ሰነዶች ሽያጭ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 4/2017(ኢዜአ)፦ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ለዕዳ ሰነዶች ሽያጭ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ከመጪው ጥር ወር 2017 ጀምሮ በይፋ ስራ እንደሚጀምር የተቋሙ ዋና ስራ አስፈፃሚ ጥላሁን ኢስማኤል(ዶ/ር) አስታውቀዋል።

ገበያው በኢትዮጵያ እያደገ ለመጣው የምጣኔ ኃብትና የፋይናንስ ፍላጎት አማራጭ እንደሚሆንም ተገልጿል።

የገበያውን ስራ መጀመር አስመልክቶ የኢትዮጵያ ሰነደ-ሙዓለ ንዋዮች ገበያ የስራ ሃላፊዎች ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የተቋሙ ዋና ስራ አስፈጻሚ ጥላሁን ኢስማኤል(ዶ/ር) ባለፈው አንድ ዓመት ኩባንያውን እውን ለማድረግ የተለያዩ ተግባራትን ሲከናወኑ መቆየታቸውን አብራርተዋል።

በአሁኑ ወቅትም ተቋሙ ስራ መጀመር የሚያስችለውን በቂ ቅድመ-ዝግጅት ያደረገ ሲሆን ካፒታል የማሰባሰብ፤ የሰው ኃይል የማደራጀት ስራ ማከናወኑን ጠቁመዋል።

በተጨማሪም የገበያውን መተዳደሪያ ደንቦች የማዘጋጀትና ለህዝብ የማስተዋወቅ ስራን ጨምሮ ገበያውን በቴክኖሎጂ መምራት የሚያስችል ግዥ መፈፀሙን አመልክተዋል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ለመንግስት የዕዳ ሰነዶች ሽያጭ ምቹ ሁኔታን የፈጠረ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

ገበያው ወደ ስራ መግባቱ ዜጎች የመንግስት የግምጃ ቤት ሰነድን በቀላሉ በመግዛት አትራፊ መሆን የሚችሉበት ሰፊ ዕድል መያዙንም ነው ያነሱት።

የሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ መጀመር መንግስት እና የግሉ ዘርፍ ለሚያከናውኗቸው ኢንቨስትመንቶች ካፒታል ለማሰባሰብ ትልቅ አቅም የሚፈጥር መሆኑን የተቋሙ ዋና ስራ አስፈፃሚ ተናግረዋል፡፡

ገበያውን በመጪው ጥር ወር 2017 ዓም ለማስጀመር ተቋማቸው ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁንም ነው ያመለከቱት።

ኢትዮ-ቴሌኮም የጀመረውን የአክሲዮን ሽያጭ ሲያጠናቅቅ በርካታ ዜጎች በገበያው ላይ ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም አንስተዋል።

በሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ አክስዮን የሚሸጡ ኩባንያዎች በየጊዜው የሂሳብ ሁኔታቸው እየተገመገመ ይፋ የሚሆንበት አሰራር መዘርጋቱንም አስታውቀዋል።

መንግስት አስተማማኝና ተወዳዳሪ ገበያ የመገንባት ዓላማ ያለው በመሆኑ ገበያው ከስጋት ነጻ እንዲሆን በትኩረት ይሰራል ብለዋል።


 

የኢትዮጵያ ሰነደ-ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ዋና ኦፕሬሽን ከፍተኛ ባለሙያ ሚካኤል ሀብቴና ከፍተኛ የቢዝነስ ባለሙያ ዮዲት ካሳ በበኩላቸው ከቴክኖሎጂ ዝግጅትና ከፍቃድ ማውጣት እንዲሁም ገበያውን ከማደራጀት አኳያ በቂ ዝግጅቶች መደረጋቸውን አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም