ቀጥታ፡

የትኛውንም አይነት ጥያቄ የሚያነሱ አካላት ለውይይትና ለሃሳብ ትግል ቁርጠኛ አቋም ሊይዙ ይገባል-የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 4/2017 (ኢዜአ):- በኢትዮጵያ የትኛውንም አይነት ጥያቄ የሚያነሱ አካላት ለሰላማዊ ውይይትና የሃሳብ ትግል ቁርጠኛ አቋም ሊይዙ ይገባል ሲሉ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን አየለ ተናገሩ።

የኢትዮጵያን ሁሉን አቀፍ የልማት ዕቅዶች ለማሳካት በመደመር እሳቤ በሕብረ ብሄራዊ አንድነት የጋራ ጥረት በመደረግ ላይ ይገኛል።

ለዚህም መንግስት በሁሉም መስክ ውጤቶችን በማስመዝገብ ሀገራዊ ልማትና ብልጽግናን ለማረጋገጥ ቁርጠኝነቱን በተግባር እያሳየ ነው።

ለኢትዮጵያ የሚገባትን እና የሚታሰበውን እድገት ለማሳካት ደግሞ ከምንም በላይ ሰላም ወሳኝ መሆኑን በርካቶች ይስማሙበታል።

ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተገናኘ ኢዜአ ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን አየለ፤ የሰላም አጀንዳ የሁላችንም ጉዳይ ነው ብለዋል።

መንግስት ተደጋጋሚ የሰላም ጥረት የሚበረታታ መሆኑን ጠቅሰው በኢትዮጵያ የትኛውንም አይነት ጥያቄ የሚያነሱ አካላት ለሰላማዊ ውይይትና የሃሳብ ትግል ቁርጠኛ አቋም ሊይዙ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው የመጡ ታጣቂዎች ውሳኔ አድንቀው፤ ለሕዝብና ለሀገር ሲባል ግጭቶችን በሰላማዊ አማራጭ ለመፍታት ሁሉም ወገኖች ቁርጠኛ ሊሆኑ እንደሚገባ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የግጭትና ጦርነትን ምዕራፍ ለመዝጋት ዕርቅና ዘላቂ ሰላምን ማስፈን፤ ትብብርና አብሮነትን ማጠናከር እንደሚገባም እንዲሁ።

የመወያየት፣ የመነጋገርና የመከባበር እሴቶቻችን ሀገራዊ ችግሮችን ለመፍታት ቁልፍ መሳሪያዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በዚህም በየትኛውም ቦታ ጥያቄ አለን የሚሉ ሃይሎች ለውይይት ለሃሳብ ትግል ቁርጠኛ አቋም ሊይዙ ይገባል ነው ያሉት።

የጋራ ምክር ቤቱም የሰላምን አማራጭ በመደገፍ ከሁሉም ጋር በቅንጅት ለመስራት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም