ቀጣና ዘለል አንድምታ ያለው የአንካራው ስምምነት - ኢዜአ አማርኛ
ቀጣና ዘለል አንድምታ ያለው የአንካራው ስምምነት

የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካ አንድምታ ከቀንዱ ሀገራት የተሻገረ ነው። የቀጣናው ሀገራት ትስስርና ትብብርም እንደዚያው። በነዚህ ሀገራት መካከል የሚፈጠር መቃረን የሚያሳድረው ተጽዕኖም አድማስ ዘለል ነው።
በቅርቡ በኢትዮጵያና ሶማልያ መካከል ተፈጥሮ የነበረው የግንኙነት መሻከር ከሁለቱ ሀገራት ባሻገር በቀጣናው ስውርና ገሀድ ፍላጎት ያላቸው የውጭ ኃይሎችን ያሳሰበና ያስጨነቀ ጉዳይ መሆኑ እሙን ነው።
በቱርክዬ ርዕሰ ከተማ አንካራ የተደረሰው የኢትዮ-ሶማልያ ሥምምነት ግን ለበርካቶች እፎይታን ይዞ መጥቷል።
ከኢትዮጵያና ሶማልያ ጋር መልካም ወዳጅነት ያላት ቱርክዬ የሁለቱን አገራት ለማሸማገል ጥረት ከጀመረች ውላ አድራለች። ምንም እንኳ ጥረትና ድካሟ በተደጋጋሚ ሳይሳካ ቢቆይም ካለፈ ሐምሌ 2016 ዓ.ም ጀምሮ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት በሚኒስትሮች ደረጃ ለማረቅ ተግታለች። በሦስተኛው ዙር በሁለቱ ሀገራት መሪዎች ደረጃ የተደረገው ድርድር ግን ፍሬ አፍርቶላታል።
ቱርክዬ እየተገነባ ባለው የብዝሃ-ዋልታ ዓለም ውስጥ ጎልተው እየወጡ ካሉ ኃያላን ሀገራት መካከል አንዷ ናት። በአፍሪካ ውስጥ ያላት ተፅዕኖ ፈጣሪነትም እያደገ መምጣቱ ይታወቃል-በተለይ በአፍሪካ ቀንድ።
ቱርክዬ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ታሪካዊና ዘርፈ ብዙ ትስስር ጠንካራ የሚባል ነው። ቱርክዬ ከቻይና ቀጥላ በኢትዮጵያ ግዙፍ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ያፈሰሰች ሀገር ናት። ከኢኮኖሚያዊ ቁርኝቱ ባሻገር ሁለቱ አገራት በፖለቲካዊና ማኅበራዊ እንዲሁም ስትራቴጂያዊ በሆኑ ጉዳዮች ያላቸው ትብብርም የላቀ ነው። ቱርክዬ ከሶማልያ ጋር ያላት አጋርነትም እየተጠናከረ የመጣ ነው።
እናም የሁለቱ ሀገራት አለመግባባት ለቱርክዬ ሳንካ ነበር። ስለዚህ የሁለቱ ሀገራት አለመግባባት በአንካራው ድርድር ዲፕሎማሲያዊ እልባት ማግኘቱ ለፕሬዝዳንት ኤርዶሃን ወሳኝ እርምጃ ሆኖላቸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የሶማልያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ በአንካራ ተገኝተው ያደረጉት ውይይት የቀንዱን ውጥረት አርግቧል። ስምምነቱ በሁለቱ ሀገሮች መካከል የተፈጠሩ አለመግባባቶችን በውይይት በመፍታት ግንኙነታቸውን ወደ አዲስ የትብብር ምዕራፍ ለመውሰድ የሚያስችል እንደሆነም ተገልጿል።
በሶማልያ በኩል ኢትዮጵያ አስተማማኝ፣ ደህንነቱ የተረጋገጠ እና ዘላቂነት ያለው የባሕር በር የማግኘት መብትን ዕውቅና ለመስጠት እና በዚህ ጉዳይ ላይ አብሮ ለመስራት መስማማት ችላለች።
በተመሳሳይ ኢትዮጵያም የሶማልያን የግዛት አንድነት ለማክበር የነበራትን የቆየ አቋም አጽንታለች። ሁለቱ ሃገራት የኢትዮጵያን የባሕር በር ፍላጎት እውን ለማድረግ በቀጣይ አራት ወራት በቱርክዬ አስተባባሪነት ዝርዝር ቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ ምክክር ለማካሄድ ተስማምተዋል።
መሪዎቹ በመግለጫቸው ኢትዮጵያ በሶማልያ የባሕር ዳርቻ በኩል ዘላቂ እና ደኅንነቱ የተጠበቀ የወደብ አማራጭ በምታገኝበት ዙሪያ የቴክኒክ ውይይቶችን ለመጀመር ይሁንታቸውን ሰጥተዋል።ይህ የወደብ አማራጮችን በስፋት ለመጠቀም ለምትፈልገው ኢትዮጵያ ትልቅ እርምጃ ተደርጎ የሚወሰድ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመግለጫቸው፤ ቱርክ በአፍሪካ ቀንድ ሠላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ለምታደርገው አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል። የኢትዮጵያና የሶማልያ ሕዝቦች በቋንቋ፣ በባህል እና በጉርብትና ብቻ ሳይሆን በደም የተሳሰሩ ወንድማማቾች እና እህታማማች ሕዝቦች መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አውስተዋል።
ይልቁንስ ሶማልያን ከአሸባሪዎች ለመከላከልና ሠላሟን ለማረጋገጥ ሲባል በሺዎች የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል አባላት በከፈሉት መስዋዕትነት ጭምር የተሳሰረ መሆኑን ነው ግልጽ ያደረጉት። ኢትዮጵያ ለጋራ ሠላምና ልማት ከሶማልያ ጋር ለመስራት ቁርጠኛ መሆኗንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል።
የሶማልያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድም ለዚህ ሀቅ ጠንካራ እማኝነታቸውን ሰጥተው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ለአገሪቱ ሠላም መጠበቅ ለዓመታት የከፈለውን ዋጋ መቼም አይዘነጋም ሲሉ የሚገባውን ክብር አጎናጽፈውታል።
ሶማልያ የኢትዮጵያ እውነተኛ ወዳጅ ሆና ትቀጥላለች ሲሉም አረጋግጠዋል። ሁለቱ ሀገራት በቀጣይም ሠላምን ለማፅናት በሚያደረጉት ጥረት መንግሥታቸው ቁርጠኛ መሆኑን ተናግረዋል።
በጥቅሉ የአንካራው የአቋም መግለጫ የሁለቱን አገራት የጋራ አሸናፊነት ያንጸባረቀ ነው። ለዘመናት በተለይም ላለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት ፈጽሞ የተዘነጋ እና የማይታሰብ ይመስል የነበረውን የኢትዮጵያን የባሕር በር ጉዳይ በድፍረት ዓለም አቀፍ አጀንዳ ለማድረግ ያስቻለ ነው።
የኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኘት ከሃገር አልፎ ለቀጣናው ሁለንተናዊ ትስስር ጭምር ወሳኝ መሆኑ መግባባት የተደረሰበት ሆኗል።
በተለያዩ አሰራሮች እና አግባቦች፣ በሠላማዊ መንገድ እና በሰጥቶ መቀበል መርህ ኢትዮጵያ አስተማማኝ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ፣ ዘላቂ የባሕር በር ሊኖራት እንደሚገባ መግባባት የፈጠረ ነው።
ይህን ሥምምነት ዕውን ለማድረግ በዝርዝር ቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ ቀጣይ ድርድሮች በማካሄድ በአጭር ጊዜ ውስጥ ገቢራዊ ለማድረግ ተጨባጭ እርምጃዎችን ለመውሰድ መግባባት ችለዋል። በዚህ ረገድ ቱርክዬ ሂደቱን ለማሳለጥ እና ለማገዝ ኃላፊነት መውሰዷ ደግሞ ዘላቂነት እንዲኖረው እንደ መልካም ዕድል የሚወሰድ ነው።
ኢትዮጵያና ሶማልያ በአንካራ የደረሱት ስምምነት ከአውሮፓ ኅብረት እስከ አፍሪካ ኅብረት እንዲሁም ከምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) እስከ ተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማትና አገራት አድናቆት የቸሩት ሆኗል።
ይህ ስምምነት የሁለት አገራት ስምምነት ብቻ አይደለም። የጥይት ድምጽ የማይሰማባት አፍሪካ የመፍጠር ህልም አካልም ጭምር ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። የውዳሴው መነሻና መድረሻውም ደግሞ ስምምነቱ የአፍሪካ ቀንድን ከግጭት አዙሪት ወጥቶ ወደ ዘላቂ ሠላምና መረጋጋት ብሎም ወደ አህጉራዊ ትብብር የሚወስድ መሆኑ ነው።
በእርግጥም ሥምምነቱ የፈረንጆቹ አዲስ ዓመት ከመባቱ በፊት ለቀንዱ አገራት የቀረበ ሥጦታ ነው። እናም የአንካራው ስምምነት ከኢትዮጵያና ከሶማልያ ባለፈ አንድምታው ቀጣናውን የተሻገረ በመሆኑ የአፍሪካውያንና የወዳጅ ሀገራት በቅን መንፈስ የተቃኘ ድጋፍ ያሻዋል።
ሠላም!