ቀጥታ፡

ለአምስት የመንግስት ሆስፒታሎች 6 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት የመድሀኒትና የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 4/2017 (ኢዜአ):- የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት 6 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት መድሀኒትና የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ ለአምስት የመንግስት ሆስፒታሎች አስረከበ።

በኡስታዝ አቡበከር አህመድ አስተባባሪነት ከሙስሊም ኤድ አሜሪካ የተደረገውን ድጋፍ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ሃጂ ኢብራሂም ቱፋ ለሆስፒታሎቹ አስረክበዋል።

ፕሬዝዳንቱ ባደረጉት ንግግር ለሆስፒታሎቹ የተደረገው ድጋፍ መተጋገዝና መረዳዳት ከተቻለ ችግሮችን መፍታት የሚቻል መሆኑን ያመላከተ ነው ብለዋል።

የአቅማችንን በማድረግ በመተጋገዝና በመረዳዳት ከሰራን ሀገርን መጥቀምና የሰዎችን ችግር ማቃለል እንችላለን ሲሉ ተናግረዋል።

ድጋፉ ለድልጮራ፣ ለአሶሳ፣ ጅግጅጋ ሆስፒታሎች እና ለሙሁር አክሊል የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል እንዲሁም ለስልጤ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል መሆኑም ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም