ዩኒቨርሲቲው በካላዛር በሽታ ላይ ያከናወነው አዲስ የምርምር ሥራ ውጤት እንደተገኘበት አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
ዩኒቨርሲቲው በካላዛር በሽታ ላይ ያከናወነው አዲስ የምርምር ሥራ ውጤት እንደተገኘበት አስታወቀ
ጎንደር፤ ታህሳስ 4/2017 ዓ/ም (ኢዜአ) የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለካላዛር በሽታ ሲሰጥ የቆየውን የመርፌ ህክምና ሙሉ በሙሉ በሚዋጥ መድኃኒት ለመተካት የጀመረው አዲስ የምርምር ስራ ውጤታማ መሆኑን አስታወቀ፡፡
የካላዛር በሽታ ሞቃታማና ቆላማ በሆኑ አካባቢዎች በስፋት የሚገኝ ሲሆን ሳንድ ፍላይ ወይም የአሸዋ ዝንብ በምትባል ትንኝ ንክሻ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍ ገዳይ በሽታ መሆኑ ይታወቃል።
በበሽታው የተያዘ ሰውም ከፍተኛ የሰውነት ሙቀት፤ የክብደት መቀነስ፤ የጣፊያ እብጠትና በአፍንጫ በኩል ደም የመፍሰስ ዋና ዋና ምልክቶች ይታዩበታል።
በበሽታው የተያዙ ሰዎችን ፈጥኖ ወደ ህክምና ተቋም ማምጣት ካልተቻለ በሽታው 90 በመቶ የሚሆኑትን ህመምተኞች ለሞት እንደሚዳርግም ተመላክቷል።
በሽታው በሰው ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስም ምርምር ሲካሄድ መቆየቱን የገለፁት በዩኒቨርሲቲው የካላዛር ህክምና ምርምር ማዕከል ኃላፊና ተመራማሪ ዶክተር መዝገቡ ሰላምሰው ናቸው።
በዚህም አዲሱ የምርምር ሂደት ታማሚዎች ሆስፒታል ተኝተው ህክምናውን እንዲከታተሉ የሚያስገድደውን የመርፌ ህክምና አሰጣጥ በአፍ በሚዋጥ መድኃኒት የሚቀይር መሆኑን ገልፀዋል።
በዚህም ታማሚዎች በሚታዘዝላቸው የሚዋጥ መድኃኒት በመታገዝ ቤታቸው ሆነው ህክምናውን በመከታተል በአጭር ጊዜ መዳን እንዲችሉ የሚያደርግ እንደሆነም ገልፀዋል።
የምርምር ሂደቱ መድኃኒቱ የሚያደርሰውን የጎንዮሽ ጉዳት ለመቀነስ የሚያግዝና ለታካሚዎችም ምቾት የሚሰጥ መሆኑን ጠቁመው፤ ምርምሩ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶ እየተከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
አዲሱ የምርምር ሂደት ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ላይ መጀመሩን ጠቁመው፤ ለምርምር ስራው የሚያግዙ ፈቃደኛ ታካሚዎችን የማስገባት ሂደቱን 60 በመቶ ማሳካት መቻሉን ተናግረዋል፡፡
በ2025 በአዲሱ የፈረንጆች ዓመት ፈቃደኛ ታካሚዎችን ሙሉ በሙሉ የማስገባት ስራው እንደሚጠናቀቅ ጠቁመው፤ መድኃኒቱ አነስተኛ የጎንዮሽ ጉዳት ያለውና ፈዋሽነቱና በሽታውን የማጥፋት ሃይሉ ከፍ ያለ ነው ብለዋል።
ከዚህ ቀደም በማዕከሉ በተካሄዱ ምርምሮች ለአንድ ወር ይሰጥ የነበረውን የህክምና ሂደት ወደ 17 ቀን በማሳጠር ህክምናው በመርፌ ሲሰጥ መቆየቱንም ጠቁመዋል፡፡
በአዲሱ ምርምር የህክምና ሂደት ደግሞ ወደ 14 ቀን ዝቅ ለማድረግ መታቀዱን ጠቁመው፤ ደረጃቸውን በጠበቁ የዲጂታል የላቦራቶሪ መሳሪያዎች በመታገዝ ምርምሩ በመካሄድ ላይ እንደሚገኝም አብራርተዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲው የኢሞኖሎጂና ሞልኪዩላር ባዮሎጂ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ሀና ዮሃንስ፤ የመድኃኒቱን አወሳሰድ በማሻሻል በረጅም ጊዜ ሂደትም አዳዲስ ክትባቶችን በምርምር ለማውጣት መታቀዱን ገልፀዋል፡፡
በቀደመው አሰራር አንድ የካላዛር ታማሚ በሽታው እንዳለበት ለማረጋገጥ ከደም መቅኒና ከጣፊያ ላይ የሚወሰደው ናሙና ከባድ ህመምና ስቃይ እንዳለው አስታውሰው፤ ይህን ችግር ለማስቀረትም ምርምር እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በምርምር ማዕከሉ የቤተ ሙከራ ክፍል ኃላፊ አቶ መክብብ ካሣ በበኩላቸው፤ በቤተ ሙከራው የካላዛር በሽታ አምጪ ህዋስ የዘረ መል ዓይነት ላይ በላቦራቶሪ መሳሪያዎች የታገዘ ምርምር እየተካሄደ ነው ብለዋል፡፡
በተጨማሪም በታማሚዎች ተፈጥሯዊ የመከላከል አቅምና ልዩነቶች ላይም የዘረ መል ምርመራ እንደሚካሄድ ጠቁመው፤ ይህም በበሽታው የተያዙ ታካሚዎች በሚሰጣቸው መድኃኒቶች ምን ያህል የጤና መሻሻሎች እንዳሳዩ ለማረጋገጥ ያግዛል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ባቋቋመው የካላዛር በሽታ ምርምርና ህክምና ማዕከል ህክምናውን በመከታተል ላይ የሚገኘው አቶ ሰጠኝ ማንዴ እንዳሉት፤ በበሽታው ተይዘው በተሰጣቸው ህክምና ጤናቸው እየተመለሰ ይገኛል።
በህክምና ማዕከሉ በተደረገለት ህክምና ከበሽታው ማገገም መቻሉን የገለፀው ደግሞ ሌላው ታካሚ ወጣት ይታየው አዲስ ነው።
የዩኒቨርሲቲው የካላዛር ምርምርና ህክምና መስጫ ማዕከል በዓመት ከ400 በላይ ለሚሆኑ የበሽታው ተጠቂዎች ነጻ የህክምና አገልግሎት እንደሚሰጥም ለማወቅ ተችሏል።