ቀጥታ፡

የአንካራው ስምምነት ከሁለቱ ሀገራት የጋራ ተጠቃሚነት ባሻገር ለቀጣናዊ ሰላምና መረጋጋት የላቀ ትርጉም አለው- ያዕቆብ አርሳኖ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 4/2017(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካከል የተደረሰው የአንካራው ስምምነት ለቀጣናው ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት የላቀ ትርጉም እንዳለው የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ያዕቆብ አርሳኖ (ዶ/ር) ገለጹ።

የአንካራ ስምምነት በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካከል የተፈጠሩ አለመግባባቶችን በውይይት በመፍታት ግንኙነታቸውን ወደ ላቀ የትብብር ምዕራፍ ለማሸጋገር የሚያስችል ነው።


 

በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁርና ተመራማሪው ያዕቆብ አርሳኖ (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የቆየ ወዳጅነትና ጥብቅ ቁርኝት ያላቸው አገራት መሆናቸውን አስታውሰዋል።

የሁለቱ አገራት ህዝቦችም ከጉርብትና ባለፈ ጠንካራ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ያዳበሩና መልከ ብዙ ማህበራዊ እሴቶችን እንደሚጋሩ ጠቅስዋል።

ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ሰላም መስዕዋትነት በመክፈል የቁርጥ ቀን አጋርነቷን እና እውነተኛ ወዳጅነቷን በተግባር ማሳየቷንም አስታውሰዋል።

ስምምነት ከሁለቱ አገራት የጋራ ተጠቃሚነትን ባሻገር ለቀጣናዊ ልማት፣ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት የላቀ ትርጉም እንዳለው ገልጸው፤ ይህም በሌሎች አገሮች ዘንድ በጥሩ ተሞክሮነት የሚወሰድ መሆኑን ነው የተናገሩት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያና የሶማሊያ ህዝቦች በባህል እና በቋንቋ የተሳሰሩ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ የጋራ ልማት ትብብራቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ወታደሮች ለሶማሊያ ሰላም የከፈሉትን መስዋዕትነት እንደማይዘነጋና በቀጣይም ሰላምን ለማፅናት በሚደረግ ጥረት መንግስታቸው በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

የተለያዩ ሀገራትና ተቋማትም የአንካራው ስምምነት የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ እውን ለማድረግ የሚያስችልና ለቀጣናው ሰላምና የጋራ ልማት ለማረጋገጥ ወሳኝ ስለመሆኑ ገልጸዋል።

በሁለቱ ሀገራት መካከል የተደረጉ ውይይቶች እና ምክክሮች ለሁለቱ ሀገራት የወደፊት መረጋጋትና መበልፀግ ወሳኝ ሚና እንደሚኖረውም እንዲሁ በመግለጫቸው አመላክተዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም