በአዲስ አበባ ከተማ ለሽብር ድርጊት ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ተጠርጣሪዎች ተያዙ - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ ከተማ ለሽብር ድርጊት ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ተጠርጣሪዎች ተያዙ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 4/2017(ኢዜአ)፦በአዲስ አበባ ከተማ የፅንፈኛውን የሽብር ቡድን ተልዕኮ ለመፈፀም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ አራት ተጠርጣሪዎች በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ክትትል በቁጥጥር ሥር ውለዋል።
በሽብር ወንጀል የተጠረጠሩት አራቱ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ሊውሉ የቻሉት በአዲስ አበባ ከተማ የሽብር ተግባር ለመፈፀም ከፅንፈኛው የሽብር ቡድን የወሰዱትን ተልዕኮ ከግብ ለማድረስ 120 የክላሽንኮቭ ጥይት እና ኤፍ ዋን ቦንብ ይዘው ሲንቀሳቀሱ እንደሆነ ፌዴራል ፖሊስ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አባላት ባደረጉት ጠንካራ ክትትል ታህሳስ 4 ቀን 2017 ዓ.ም ተጠርጣሪዎቹ እጅ ከፍጅ ተይዘው ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሚገኝ የምርመራ ቡድኑ መግለጹን ከፌዴራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ሕብረተሰቡ እስከ አሁን እያደረገ ላለው ተሳትፎ ምስጋና እያቀረበ፣ ተመሳሳይ የወንጀል ተግባር ሲመለከት የዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያን (EFPApp) በመጠቀም ወይም በነፃ የስልክ መስመር 991 በመደወል በፍጥነት ጥቆማ በመስጠት ወይም መረጃውን በአካባቢው ለሚገኙ የፀጥታና ደኅንነት አካላት በአካል በማድረስ የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርቧል።