ክልሉ ችግሮችን በመቋቋም የጤና ስርዓቱን ማጠናከር የሚያስችሉ ስራዎችን እያከናወነ ነው - ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ - ኢዜአ አማርኛ
ክልሉ ችግሮችን በመቋቋም የጤና ስርዓቱን ማጠናከር የሚያስችሉ ስራዎችን እያከናወነ ነው - ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ
ባህር ዳር፤ ታህሳስ 3/2017(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል በችግር ውስጥ ተሁኖም የጤና አገልግሎት ስርዓቱን ለማጠናከር ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለፁ።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ከጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ እና ከሌሎች አመራሮች ጋር በክልሉ ወቅታዊ የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ማምሻውን ተወያይተዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅቱ እንደገለጹት ክልሉ በችግር ውስጥ ሁኖም ለጤናው ዘርፍ የተሻለ በጀት በመመደብና ክትትልና ድጋፍ በማድረግ አገልግሎቱን ለማቀላጠፍና የመልሶ ግንባታ ስራን ለማከናወን ጥረት እያደረገ ይገኛል።
የጤና ሚኒስቴር ድጋፎችን እያደረገ መቆየቱን አስታውሰው፤ ነገር ግን ከችግሩ ስፋት አንፃር አሁንም ጠንካራ ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ድጋፉም የበሽታ ስርጭትን የመከላከል አቅምን ማሳደግ በሚያስችል አግባብ ሊከናወን እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ፣ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትና ሌሎች አመራሮች በክልሉ የጤና ጉዳይ ላይ በመምከር ድጋፋቸውን ለማሳደግ በመምጣታቸው አመስግነዋል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በበኩላቸው፤ ክልሉ በተደራራቢ ችግር ውስጥ ሁኖ የጤና ተቋማት አገልግሎት እየሰጡ መገኘታቸው ቀደም ብሎ የማይበገር የጤና ስርዓት ለመገንባት የተደረገ ጥረት መኖሩን ማሳያ ነው ብለዋል።
ከዚህ ቀደም የተጎዱ የጤና ተቋማትን መልሶ ለማቋቋምና የዲጂታል የጤና ስርዓት እንዲኖር ሚኒስቴሩ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱንና በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በተለይም የተጠናከረ የግብዓት አቅርቦት፣ የባለሙያ አቅም ግንባታና በቴክኖሎጂ የተደገፈ የአገልግሎት አሰጣጥን የበለጠ ማስፋት የሚያስችሉ ድጋፎች እንደሚደረጉም አስታውቀዋል።
የክልሉ መንግስት ለጤናው ዘርፍ የሰጠው ትኩረት፣ ተባብሮና ተቀናጅቶ የመስራት ልመዱ የሚያስመሰግን መሆኑን ጠቅሰው፤ ቀጣይም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አንስተዋል።
ውይይቱ ያሉ ችግሮችን ለመለየትና ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ላይ የበለጠ አፅንኦት ሰጥቶ ለመስራት በማሰብ መከናወኑንም አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ሀይሉ በበኩላቸው፤ የክልሉ አመራር የጤና ስርዓቱን ለማሻሻል ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ በመስራት ተጨባጭ ስራ እየሰራ ነው ብለዋል።
በችግር ውስጥ ተሁኖም የሚከሰቱ ወረርሽኞችን ፈጥኖ በመቆጣጠር የሚያስመሰግንና በአርአያነት የሚጠቀስ ተግባር መሆኑን አረጋግጠዋል።
ለዚህ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠልም ኢንስቲትዩቱ እያደረገ ያለውን ሁለንተናዊ ድጋፍና ትብብር እንደሚያጠናክር አስታውቀዋል።
ማምሻውን በተከናወነው ውይይት የክልልና የፌደራል የዘርፉ አመራሮች ተሳትፈዋል።