ቀጥታ፡

በመዲናዋ የኮሪደር ልማቶችን ደህንነት እና ዘላቂነትን በማስጠበቅ ረገድ ስኬታማ ሥራዎች ተከናውነዋል-ግብረ ኃይሉ

አዲስ አበባ፤ታህሳስ 3/2017(ኢዜአ)፦በአዲስ አበባ ባለፉት ወራት የኮሪደር ልማቶችን ደህንነት እና ዘላቂነትን በማስጠበቅ ረገድ ስኬታማ ሥራዎች መከናወናቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ኮሪደር መሰረተ ልማት ጥበቃ የጋራ ጥምር ግብረ ኃይል አስታወቀ።

የአምስት ሴክተር መስሪያ ቤቶች ጥምረት የሆነው ግብረ ኃይሉ በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ 5 ወራት በኮሪደር መሰረተ ልማቶች የሚፈጸሙ የደንብ ጥሰቶች ለመከላከል የተከናወኑ ተግባራትን አፈጻጸም ገምግሟል።

ሴክተር መስሪያ ቤቶች በኮሪደር መሰረተ ልማቶች ላይ ጥበቃ የማድረግ እንዲሁም የደንብ ጥሰቶችን ተከታትሎ የእርምት እርምጃዎች እንዲወሰዱ ማድረግ ላይ በቅንጅት እየሰሩ ነው።

የአምስት ወራት አፈጻጸማቸውን በጋራ የገመገሙ ሲሆን የተገኙ ስኬቶች፣ የታዩ ጠንካራ ጎኖች፣ ችግሮችና መፍትሔዎች ላይ ያጠነጠነ ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የግብረ ኃይሉ ሰብሳቢ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ እንደተናገሩት፤ በመዲናዋ የተዘረጉ የኮሪደር መሰረተ ልማቶችን ዘላቂነት ለማረጋገጥ ቅንጅታዊ አሰራሮችን ማጠናከር ፋይዳው ከፍ ያለ ነው።

የሴክተር መስሪያ ቤቶቹ በጋራ ወደ ሥራ መግባታቸውን አስታውሰው፤ በመሰረተ ልማት ላይ የሚገጥሙ ችግሮችን በመለየት የመፍትሔ እርምጃዎች እየተወሰደ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ከፍጥነት ወሰን በላይ በማሽከርከር በመሰረተ ልማቶች ላይ ጉዳት ማድረስ፣የብስክሌት እና በእግረኞች መንገዶች እንቅስቃሴን አለማክበር እና በተከለከለ ቦታ መኪና ማቆምና የቆሻሻ አወጋገድ ችግሮች ይስተዋሉ እንደነበር አውስተዋል።

ለችግሮቹ ዘላቂ መፍትሔ ለማበጀት ኅብረተሰቡ በሚንቀሳቀስበት አካባቢ እንዲሁም በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን አውታሮች ግንዛቤ እንዲጨብጡ ማድረግ መቻሉን አብራርተዋል።

በዚህም የኮሪደር መሰረተ ልማቶችን ደህንነት ማስጠበቅ ላይ አወንታዊ ውጤቶች እየተገኙ ነው ብለዋል።

ደንብ ተላልፈው በተገኙ አካላት ላይ የገንዘብ መቀጮ እርምጃዎችም፤ ባለፉት አምስት ወራት በቅጣት የተሰበሰውን 103 ሚሊዮን ብር ለመንግሥት ገቢ መደረጉን አስረድተዋል።

የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ክበበው ሚደቅሳ እንደገለጹት፤ግብረ ኃይሉ ወደ ሥራ መግባቱን ተከትሎ በቅንጅት በተከናወኑ ተግባራት የትራፊክ ፍሰቱን ማሳለጥ መቻሉን ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ጽዳት አስተዳደር ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙላት ተገኝ በበኩላቸው ጽዳትን በተመለከተ በየአካባቢው ግንዛቤ ማስጨበጥ ተግባራት በመከናወኑ የማኅበረሰቡ ሕግ የማክበር ባህሉ እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።

ከተማዋ ጽዱ በማድረግ የተገኙ ውጤቶችን በላቀ ደረጃ ለማስቀጠል ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መሥራቱን እንደሚያጠናክር አረጋግጠዋል።

በከተማ ደረጃ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለሥልጣን፣ የትራፊክ ማኔጅንት፣ ጽዳት አስተዳደር ኤጀንሲ፣ የግንባታ ፈቃድ እንዲሁም የአዲስ አበባ የመብራት መሰረተ ልማት አገልግሎት በጋራ ለመስራት ከአምስት ወራት በፊት ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል።

See insights

Boost a post

All reactions:

44

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም