የደቂቅ ህዋሳትን በመጠቀም የግብርና ምርት፣ ምርታማነትና ጥራትን የሚያሳድግ የ400 ሺህ ዩሮ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ - ኢዜአ አማርኛ
የደቂቅ ህዋሳትን በመጠቀም የግብርና ምርት፣ ምርታማነትና ጥራትን የሚያሳድግ የ400 ሺህ ዩሮ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ
አዲስ አበባ፤ታህሳስ 3/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የደቂቅ ህዋሳትን ሃብት በመጠቀም የግብርና ምርት፣ምርታማነትና ጥራትን የሚያሳድግ የ400 ሺህ ዩሮ ፕሮጀክት ይፋ አደረገ።
ኢንስቲትዩቱ ከባዮና ኢመርጂንግ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት፣ ከአርባምንጭ ዩኒቨርስቲ እና ከሰበታ አግሮ ኢንዱስትሪ “በባዮቡስት” ቴክኖሎጂ ዘርፍ በጋራ ለመስራት የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል።
የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ንጉሴ ደቻሳ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ በዕፅዋት፣ እንስሳት፣ አፈር፣ ውሃ፣ አየር እና ሌሎች ደቂቅ ህዋሳት የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ ምርምር እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ በስፋት የሚገኘውን የደቂቅ ህዋስ ብዝሃ ህይወት በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል ወደ ሥራ መገባቱን ተናግረዋል፡፡
የግብርና ምርታማነትና ጥራትን ለማሳደግ በምርምርና ሌሎችም መስኮች ትብብራቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አንስተዋል።
በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የባዮ ቴክኖሎጂ ምርምር ዳይሬክተር ዶክተር ደጀኔ ግርማ እንደተናገሩት፤ ፕሮጀክቱ ናሽናል ሴንቴር ፎር ጀኔቲክ ኢንጂነሪንግ ባዮ ቴክኖሎጂ ከተባለ ጣሊያን ሀገር ካለ ድርጅት በተገኘ የ400 ሺህ ዩሮ ድጋፍ ለሁለት ዓመታት የሚተገበር ነው።
ፕሮጀክቱ እስከ ስድስት ወር የሚፈጅ የእንሰት የማምረት ሂደትን ወደ 28 ቀን ዝቅ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
እንደዚሁም ወተትን ለማርጋት፣ ሳይበላሽ እንዲቆይና ጥራቱን ጠብቆ ለገበያ ለማቅረብ የሚያስችሉ ደቂቅ ህዋሳትን ለማምረትም ያለመ ነው ብለዋል።