ሁሉን አቀፍ የጤና ሽፋን ተደራሽነትን ለማስፋት ቅንጅታዊ አሰራር ተጠናክሮ መቀጠል አለበት - ኢዜአ አማርኛ
ሁሉን አቀፍ የጤና ሽፋን ተደራሽነትን ለማስፋት ቅንጅታዊ አሰራር ተጠናክሮ መቀጠል አለበት
አዲስ አበባ፤ታህሳስ 3/2017(ኢዜአ)፦ሁሉን አቀፍ የጤና አገልግሎት ሽፋን ተደራሽነትን ለማስፋት ባለድርሻ አካላት ከመንግስት ጋር ያላቸውን ቅንጅት አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው የጤና ሚኒስቴር ገለፀ።
ሁሉን አቀፍ የጤና ሽፋን ቀን "የመንግስት አገልግሎት ለጤና" በሚል መሪ ሀሳብ ከህዳር 30 ቀን 2017 ጀምሮ በተለያዩ መርሃ ግብሮች እየተከበረ ሲሆን በዛሬው እለትም የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።
በጤና ሚኒስቴር የስራ አመራር ዋና ስራ አስፈፀሚ ዶክተር አስናቀ ዋቅጅራ በዚህ ወቅት እንዳሉት፥ በዘላቂ የልማት ግቦች ከተመላከቱ 17 ግቦች መካከል አንዱ የጤና ጉዳይ ሲሆን የጤና አገልግሎት ተደራሽነት ለዚህ ግብ መሳካት ወሳኝ ነው።
መንግስት የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋት በማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህንና የህክምና ተቋማት ግንባታ እንዲሁም የጤና ባለሙያዎች ስልጠና ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
ሁለንተናዊ የጤና ሽፋንን ለማሳካት ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት፣ ማህበረሰቡን ማንቃትና ማብቃት እንዲሁም ጤናን በሁሉም ፖሊሲ ማካተት ወሳኝ መሆናቸውን ገልፀዋል።
በኢትዮጵያ ባለፉት አመታት የመጀመሪያ ደረጃ የጤና ክብካቤ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግና የአገልግሎት ሽፋንን ለማሻሻል ሲከናወኑ የቆዩ በርካታ ስራዎች ተጨባጭ ውጤት እንደተገኘባቸው ተናግረዋል።
በቅርቡ የተከለሰው የአገሪቱ የጤና ፖሊሲ በሽታ መከላከል ላይ ያተኮረ ጥራቱን የጠበቀ የህክምና አገልግሎት በመስጠትና የማይበገር የጤና ስርዓት በመገንባት ሁሉ አቀፍ የጤና ሽፋን ማሳደግን ዓላማ ያደረገ እንደሆነም አስረድተዋል።
ሁሉን አቀፍ የጤና ሽፋንን ለማሳደግ በ2016 በጀት አመት በቤተሰብ እቅድ፣የእናቶችና አፍላ ወጣቶች ጤና፣በቲቢና ኤች አይቪ/ኤድስ ፕሮግራም፣ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን መከላከልና የጤና መድህን ሽፋን አበረታች ውጤት መመዝገቡን ገልፀዋል።
የመጀመሪያ ደረጃ የጤና አገልግሎት ተደራሽነት አመርቂ ውጤት የተመዘገበበትና ሽፋኑም 95 በመቶ መድረሱን አስረድተዋል።
አጠቃላይ የሁለተኛ ደረጃ የጤና አገልግሎት ተደራሽነት ሽፋንም ከ75 በመቶ በላይ መሆኑን ጠቅሰው፥ የሪፈራል ትስስርን የማጠናከር ስራ በትኩረት የሚሰራ እንደሆነም ተናግረዋል።
በቀጣይም በተለይ የህፃናት ስርዓተ ምግብና የህብረተሰብ ድንገተኛ የጤና አደጋዎች ርብርብ የሚጠይቁ ስራዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
ከንጥረ ምግብ ጋር ተያይዞ የተሰሩ በርካታ ስራዎች ቢኖሩም አሁንም ቀሪ ስራዎች መኖራቸውንም ነው የተናገሩት።
ከሚመለከታቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ጋር በመሆን የውሃ አቅርቦትና ሌሎች መሟላት በሚገባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ሁሉን አቀፍ የጤና ሽፋን በየአመቱ በአለም አቀፍ ደረጃ የሚከበረው በጉዳዩ ላይ ያለን ግንዛቤ ለማሳደግና ይህን ለማሳካት የሚያስፈልገውን ቁርጠኝነት ለመፍጠር በማሰብ ነው ብለዋል።
የተለያዩ አለም አቀፍ ድንጋጌዎች ዜጎች የኑሮ ሁኔታቸው ሳያግዳቸው መሰረታዊ የጤና አገልግሎትን ማግኘት እንዳለባቸው እንደሚያትቱና መንግስት እነዚህን አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።
የተያዘውን የጤና ግብ ለማሳካት የመንግስትና ሌሎች አጋር አካላት ሚና ወሳኝ በመሆኑ ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጠይቀዋል።
የውይይት መድረኩ በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ የጤና ሽፋንን እውን ለማድረግ፣ግብዓቶችን ለማሰባሰብና ትብብርን ለማጠናከር እንደሚረዳ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የተከለሰው የጤና ፖሊሲ ለሁሉን አቀፍ የጤና አገልግሎት ተደራሽነት ትኩረት መስጠቱን የተናገሩት ደግሞ የአለም ጤና ድርጅት ተወካይ ኢኖሰንት ኮማኬች ናቸው።
የአለም ጤና ድርጅት ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ እያከናወነች ላለችው ተግባር የሚደረገውን ትብብር አጠናክሮ ይቀጥላልም ነው ያሉት።
ሁሉን አቀፍ የጤና ሽፋን ታህሳስ 6 ቀን 2017ዓ.ም በሚደረግ የእግር ጉዞ ይጠናቀቃል ተብሏል።
See insights
Boost a post
All reactions:
1919



