በገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ የተመራ የሥራ ኃላፊዎች ቡድን በስልጤ ዞን የተለያዩ የልማት ስራዎችን ተመለከተ - ኢዜአ አማርኛ
በገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ የተመራ የሥራ ኃላፊዎች ቡድን በስልጤ ዞን የተለያዩ የልማት ስራዎችን ተመለከተ
ወራቤ ፤ታህሳስ 3/2017 (ኢዜአ):- በገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ የተመራ የሥራ ኃላፊዎች ቡድን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በስልጤ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎችን ተመለከተ።
በሚኒስትሩ የተመራ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ቡድን በዞኑ በምስራቅ ስልጤ ወረዳ የተለያዩ የልማት ስራዎችን ተዘዋውሮ ተመልክቷል።
የምስራቅ ስልጢ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሳሎ ፋኒ እንዳሉት ወረዳው በበጋ መስኖ በዓመት ሶስቴ ለማምረት የሚያስችል ምቹ ስነ ምህዳር ያለበት አካባቢ ነው።
በዘንድሮው በጋ በወረዳው መስኖ የልማት ስራ 870 ሄክታር ለማልማት ታቅዶ በሽንብራ፣ በሸንኮራ አገዳና ሽንኩርትን ጨምሮ በፀደይ ሰብሎች ማልማት መቻሉንም ተናግረዋል።
በወረዳው እየተከናወነ ባለው የበጋ መስኖ ልማት ከ770 በላይ አርሶ አደሮች እየተሳተፉ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በአጠቃላይ እየለማ ካለው የበጋ መስኖ ግብርና ልማት ስራ ከ4 ሺህ 500 ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅም ገልጸዋል።
አመራሮቹ በወረዳው ምዕራብ ቆጪና ሰዳጎራ ቀበሌዎች በ45 ሄክታር መሬት ላይ እየለማ ያለውን የሙዝ ምርት ጎብኝተዋል።
እንዲሁም በተደራጁ ወጣቶች በጥምር ግብርና በ10 ሄክታር ማሳ ላይ አትክልትን ጨምሮ ሌሎች የተለያዩ ሰብሎች እየለማ ያለውን ማሳን ተመልክተዋል ብለዋል።
በወረዳው በጎርፍ ለሚፈናቀሉ ወገኖች መጠለያነት የሚያገለግሉ በማህበረሰብ ተሳትፎ እየተገነቡ የሚገኙ ቤቶችንም እንዲሁ።
በዞኑ በስልጢ ወረዳና በቅበት ከተማ አስተዳደር በሌማት ትሩፋት እየተተገበረ የሚገኝን የዶሮ እርባታና የእንስሳት ተዋፅኦ የልማት ስራዎችን ቡድኑ ምልከታ አድርጓል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ልዩ አማካሪ አቶ ንጉሴ አስረስን ጨምሮ ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ አመራር አባላት ተሳትፈዋል።