ቀጥታ፡

ህዝብን ለምሬት የዳረጉ የኤሌክትሪክ መቆራረጥ መንስኤ የሆኑ ችግሮችን ለመቅረፍ ወደ ተግባር ተገብቷል-የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት

አዲስ አበባ፣ ታህሣሥ 3/2017 (ኢዜአ)፡- ህዝብን ለምሬት የዳረጉ የኤሌክትሪክ መቆራረጥ መንስኤ የሆኑ ችግሮችን በመለየት  በዘላቂነት ለመቅረፍ ወደ ተግባር መገባቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።

አገልግሎቱን በበላይነት የሚያስተዳድረው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በበኩሉ ተቋሙ ህዝብን በጥራት ማገልገልና ትርፋማነቱን የማስቀጠል ተልዕኮውን በአግባቡ እንዲወጣ እየተሰራ መሆኑን ገልጿል።

የኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዋና ስራ አስፈጻሚ ብሩክ ታዬ (ዶ/ር)፥ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት  የፋይናንስ አስተዳደሩ ጥራት ያለው ቢሆንም በአገልግሎት አሰጣጡ አሁንም ህዝብ በምሬት የሚያነሳው መሆኑን ተናግረዋል።

የኤሌክትሪክ መቆራረጥ በህብረተሰቡ ከፍተኛ ቅሬታ እያስነሳ መሆኑን በማንሳት ዘላቂ መፍትሔ ለማበጀት የችግሩ መንስኤ መጠናቱን አንስተዋል።

በጥናቱ መሰረት ከ47 በመቶ በላይ የኃይል መቆራረጥ መንስኤ የሆነው ዛፍ በኤሌክትሪክ መስመር ላይ በመውደቅ መሆኑን አመላክተዋል።

የኤሌክትሪክ ምሶሶ ማርጀት፣ የኤሌክትሪክ ገመድ በአግባቡ አለመዘርጋትና ሌሎችም አነስተኛ ተፅዕኖ ያላቸው ምክንያቶች መለየታቸውንም ጠቅሰዋል።

ችግሮችን በመፍታት የህብረተሰቡን ጥያቄ ለመመለስ ወደ ተግባር መገባቱን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሽፈራው ተሊላ በበኩላቸው፥ ከደንበኞች የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት በቴክኖሎጂ የተደገፈ አሰራር መተግበር መጀመሩን አንስተዋል።

ከተቋማዊ አገልግሎት አሰጣጥና ከሠራተኛ ስነምግባር አንጻር ተገልጋዮች የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች ለመፍታት የግልፅነትና የተጠያቂነት ስርዓት መዘርጋቱን ጠቁመዋል።

ለደንበኞች በቅርበት አገልግሎት ለመስጠት የማሻሻያ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።

የኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዋና ስራ አስፈጻሚ ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) ተቋሙ የበለጠ አገልግሎቱን እንዲያሳልጥ ከመንግስት ድጋፍ እየተደረገለት መሆኑን ተናግረዋል።

አገልግሎቱ በትርፋማነቱና በፋይናንስ ሪፖርት ጥራቱ ያለውን በጎ ስም በአገልግሎት አሰጣጡ የሚታዩ ጉድለቶችን በማረም  እንዲደግመው ይሰራል ብለዋል።


 

አቶ ሽፈራው የህዝቡን የትራንስፎርመር ጥያቄ በፍጥነት ለመመለስ አቅርቦት ማሻሻል ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

ለዚህም በሀገር ውስጥ  አምራች ኢንዱስትሪዎች በጥራትና በከፍተኛ መጠን በማምረት ለተጠቃሚዎች እየቀረበ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ አሁን ላይ የኤሌክትሪክ ተደራሽነት 54 በመቶ ሲሆን በ2030 ለሁሉም ማህበረሰብ ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም