ቀጥታ፡

በአገር አቀፍ ደረጃ እየተከናወኑ የሚገኙ ትልልቅ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ለቱሪዝም ዘርፉ ትልቅ መነቃቃትን የሚፈጥሩ ናቸው

መቱ፤ ታህሳስ 3/2017 (ኢዜአ)፡- በአገር አቀፍ ደረጃ እየተከናወኑ የሚገኙ ፕሮጀክቶችና ትልልቅ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ለቱሪዝም ዘርፉ መነቃቃትን የሚፈጥሩ መሆናቸውን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጂጌ (ዶ/ር) ገለጹ።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጂጌ (ዶ/ር) የተመራ የመንግሥት የሥራ ሃላፊዎች ቡድን በኢሉባቦር ዞን በመከናወን ላይ ያሉ የልማት እንቅስቃሴዎችን እየጎበኙ ናቸው። 


 

በዞኑ በቾ ወረዳ የሚገኘውን የሶር ፏፏቴን የጎበኙት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትሩ፣ እንደ ሶር ፏፏቴ ያሉ ትልልቅ የቱሪስት መስኅቦችን ለማልማትና ለማስተዋወቅ በወረዳው፣ በዞኑና በክልል ደረጃ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ብለዋል።

በአገር አቀፍ ደረጃ እየተከናወኑ የሚገኙ ፕሮጀክቶችና ትልልቅ የመሠረተ ልማቶች ግንባታ ለቱሪዝም ዘርፉ መነቃቃትን የሚፈጥሩ መሆናቸውን በመግለጽ። 

በፌዴራል መንግስት በዞኑ እየተገነቡ የሚገኙ እንደ መቱ አየር ማረፊያና ሌሎች የመንገድ መሠረተ ልማቶችም መስህቦቹን ለቱሪስት መዳረሻነት ምቹ ለማድረግ ስለሚያግዙ ትኩረት ተሰጥቷቸው እንደሚሰሩ አመልክተዋል።


 

በኢሉባቦር ዞን 44 የሚደርሱ ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊና ባሕላዊ የቱሪስት መዳረሻዎች ተለይተው በወረዳና ዞን አቅም የማስተዋወቅ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የኢሉባቦር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳልካቸው ተፈሪ በጉብኝቱ ወቅት ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም