ቀጥታ፡

ጀርመን በሴቶችና ወጣቶች ተጠቃሚነት እና የማህበራዊ ጥበቃ ስርዓትን ለማጠናከር ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር እንደምትሰራ ገለጸች

አዲስ አበባ፣ ታህሣሥ 3/2017 (ኢዜአ) ጀርመን የሴቶችና የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና የማህበራዊ ጥበቃ ስርዓትን ለማጠናከር ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር እንደምትሰራ ገለጸች ፡፡

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ከጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የውጭ ፖሊሲ አምባሳደር ጌሳ ብራቲጋም ከተመራው ልዑክ ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸው ሴቶች በሰላምና ደህንነት፣ በብሔራዊ ምክክር እና በሽግግር ፍትህ ሂደት ውስጥ ያላቸውን ሚናና ተሳትፎ ማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል።

በተለይም በስርዓተ ፆታ ዕኩልነት፣ ሴቶችንና ወጣቶችን በማብቃት እንዲሁም የማህበራዊ ጥበቃ ስርዓትን በማጠናከር ዙሪያም ተነጋግረዋል።

ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር) እንዳሉት፤ ሴቶች በሀገራዊ ምክክርና በሽግግር ፍትህ ሂደት ውስጥ ጉልህ ሚና እና ተሳትፎ እንዲኖራቸው መንግስት ሰፊ ስራ እየሰራ ነው።

በተለይም በሴቶች መብት ጥበቃና ኢኮኖሚያ ተጠቃሚነት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት  እየሰራ ስለመሆኑ ነው ያነሱት።

በዚህም የጀርመን መንግስት ድጋፍ እንዲያደርግ መጠየቃቸውን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

አምባሳደር ጌሳ ብራቲጋም በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ መንግስት የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተከናወኑ ተግባራትን አድንቀዋል።


 

በተለይም ሴቶችና ወጣቶችን ለማብቃትና የማህበራዊ ጥበቃ ስርዓት ለማጠናከር ሀገራቸው በትብብር እንደምትሰራ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም