ቀጥታ፡

በሚቀጥሉት አስር ቀናት የበጋው ደረቅ፣ጸሐያማና ነፋሻማ የአየር ሁኔታ በአብዛኛው የአገሪቱ አካባቢዎች ላይ ተጠናክሮ ይቀጥላል

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 3/2017(ኢዜአ)፦ በሚቀጥሉት አስር ቀናት የበጋው ደረቅ፣ጸሐያማና ነፋሻማ የአየር ሁኔታ በአብዛኛው የአገሪቱ አካባቢዎች ላይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ የሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዮት አስታወቀ።      

የሌሊትና የማለዳው ቅዝቃዜ በተለይ በሰሜን ምስራቅ፣በሰሜን፣በምስራቅና በደቡብ ደጋማ የአገሪቱ አካባቢዎች ላይ ቀጣይነት እንደሚኖረውም አስታውቋል።

ከሳይቤሪያ ከፍተኛ የአየር ግፊት ላይ በመነሳት ወደ አገራችን የሚነፍሰው ደረቅ እና ቀዝቃዛ የአየር ሁኔታ በሚቀጥሉት ቀናት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የአየር ትንበያ መረጃዎች ያመላክታሉ ብሏል። 

በሌላ በኩል በጥቂት የምዕራብና የደቡብ ምዕራብ ላይ የደመና ሽፋን እንደሚኖራቸው ኢንስቲትዩቱ ለኢዜአ በላከው የአየር ሁኔታ ትንበያ አስታውቋል።

በምዕራብ፣በደቡብ ምዕራብ በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው በሆኑት የአገሪቱ ክፍሎች አነስተኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ ይጠበቃል ብሏል። 

በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍሎች የሚኖረው ደረቅ የእርጥበት ሁኔታ ለመኸር ሰብል ስብሰባ ተግባራትን ለማከናወን አመቺ ሁኔታን እንደሚፈጥር ኢኒስቲትዩቱ ጠቁሟል።

በሌላ በኩል በሰሜን፣በሰሜን ምሰራቅ፣በመካከለኛውና ደቡብ ደጋማ አካባቢዎች የሌሊትና የማለዳው ቅዝቃዜ በአንጻራዊ ሁኔታ የሚጠናከር ሲሆን ይህም ለቋሚ ተክሎች፣በጓሮ አትክልትና በመስኖ ለሚለሙ ሰብሎች እድገት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊኖረው ይችላል ብሏል።  

ደጋ ሁለተኛ ወቅታቸው ለሆኑ አካባቢዎች የሚኖረው እርጥበት በተለያየ እድገት ደረጃ ላይ ለሚገኙ ሰብሎችም ሆነ ለግጦሽ ሳርና ለመጠጥ ውሃ አቅርቦት በጎ ጎን እንደሚኖረው ተገልጿል።

በዚሁ ወቅት በአብዛኞቹ ተፋሰሶች ደረቅ ሆነው እንደሚቆዩ የሚጠበቅ ቢሆንም በጥቂት ተፋሰሶች ላይ መጠነኛ እርጥበት እንደሚያገኙ ይጠበቃል ነው ያለው ኢኒስትቲዩቱ።

ባሮ አኮቦ፣የመካከለኛ እና ታችኛው ኦሞ ጊቤና ስምጥ ሸለቆ ተፋሰሶች መጠነኛ እርጥበት የሚያገኙ ሲሆን ሌሎች ደረቅ ሆነው እንደሚቆዩም አስታውቋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም