11ኛው ሀገር አቀፍ የጥራት ሽልማት የፊታችን ቅዳሜ ይካሄዳል - ኢዜአ አማርኛ
11ኛው ሀገር አቀፍ የጥራት ሽልማት የፊታችን ቅዳሜ ይካሄዳል
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 3/2017(ኢዜአ)፡- 11ኛው ሀገር አቀፍ የጥራት ሽልማት የፊታችን ቅዳሜ በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ የጥራት ሽልማት ድርጅት ገለጸ።
የኢትዮጵያ የጥራት ሽልማት ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ ቴዎድሮስ መብራት ስለሽልማቱ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም 11ኛው ሀገር አቀፍ የጥራት ሽልማት የፊታችን ቅዳሜ ታህሣሥ 5 ቀን 2017 ዓ. ም ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት በአዲስ አበባ የሚካሄድ መሆኑን ገልጸዋል።
ለጥራት ልዩ ትኩረት በመስጠትና የሽልማት ስርዓትን በመዘርጋት የሀገሪቱን ተቋማትና ድርጅቶች ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም ባለፉት 10 ዓመታት የሽልማት መርሐ ግብር በማዘጋጀት ለተቋማት እና ድርጅቶች እውቅና መስጠቱን አስታውሰዋል።
የፊታችን ቅዳሜ በሚካሄደው 11ኛው የሽልማት መርሐ ግብርም በአምራች፣ በአገልግሎት ዘርፍ፣ በፐብሊክ ሰርቪስና በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰማሩ ድርጅቶችና ተቋማት እውቅና እና ሽልማት እንደሚሰጣቸው ይጠበቃል።