ቀጥታ፡

በላሊበላ ከተማ የሚከበረው የዘንድሮው የገና በዓል ቱሪዝሙን ለማነቃቃት እድል ይፈጥራል


ወልዲያ፤ ታህሳስ 3/2017(ኢዜአ)፦ በሰሜን ወሎ ዞን ላሊበላ ከተማ የሚከበረው የዘንድሮው የገና በዓል የቱሪዝም ዘርፉን ለማነቃቃት እድል እንደሚፈጥር የዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ አስታወቀ።

በዓሉን በድምቀት ለማክበር አብይና ንዑሳን ኮሚቴዎችን በማዋቀር ወደ ሥራ መገባቱም ተገልጿል።

የኢትዮጵያውያንን የቆየ ስልጣኔ ከሚያሳዩ ቋሚ ምስክሮች አንዱ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያን ነው።

ላሊበላ በበዓላት ሰሞን በደማቅ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ድባቦች ደምቆ ይውላል።

በተለይም የገና በዓል በላሊበላ በተለየ ሃይማኖታዊ ትዕይንቶች ታጅቦ እና ደምቆ ይከበራል።

ይህም የታሪካዊቷን ከተማ የሀገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶች ፍሰት በእጅጉ ይጨምራል።

የሰሜን ወሎ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ገነት ሙሉጌታ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ ታህሳስ 29 የሚከበረውን የገና በዓል በላሊበላ ከተማ በድምቀት ለማክበር ከወዲሁ ዝግጅት እየተደረገ ነው።

ይህም በተለያዩ ምክንያቶች የተቀዛቀዘውን የከተማዋን የቱሪዝምና ንግድ እንቅስቃሴ ለማነቃቃት ጥሩ እድል እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

ችግሩን ለመፍታት በተሰሩ ስራዎች መሻሻል በመታየቱ ይህን አጋጣሚ በመጠቀም የዘንድሮውን የገና በዓል በተሻለ ድምቀት ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑም ተመላክቷል።

ለበዓሉ ስኬታማነት የመስተንግዶ፣ የመሠረተ ልማት፣ የገቢ አሰባሰብ፣ የሠላምና ፀጥታ፣ እንዲሁም የህዝብ ግንኙነትና ሌሎች ኮሚቴዎችን በማዋቀር ወደ ስራ መገባቱን ሃላፊዋ ገልፀዋል።

በዓሉ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ይዘቱን ጠብቆ በድምቀት እንዲከበር ኮሚቴው እየሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

በዘንድሮው በዓል አከባበር ሁለት ሺህ የውጭ ቱሪስቶችና 640 ሺህ የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች በዓሉን ይታደማሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም እንዲሁ።

ከጎብኚዎችም 283 ሚሊዮን 928 ሺህ ብር ገቢ ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ሃላፊዋ ገልፀዋል።

የበዓሉ መከበር በተለያየ ምክንያት ተቀዛቅዞ የቆየውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ለማነቃቃት ከማገዙም በላይ የአካባቢውን ማህበረሰብ በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ አመልክተዋል።

ካለፈው ሐምሌ ወር 2016 ዓ.ም እስከ ህዳር ወር 2017 ዓ.ም አጋማሽ ድረስ 2 ሺህ 406 የውጪ ቱሪስቶች ላሊበላን መጎብኘታቸውን ጠቅሰው፤ ከእነዚህም ከ13 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን ገልፀዋል።

በአካባቢው የተረጋጋ ሰላም የተፈጠረ በመሆኑ የሀገር ውስጥና የውጪ ጎብኝዎች የዘንድሮውን የገና በዓል ለማክበር በላሊበላ ከተማ እንዲታደሙ ጥሪ አቅርበዋል።

የደብረ ሮሃ ቅዱስ ላሊበላ ገዳም ዋና አሰተዳዳሪ ቆሞስ መምህር አባ ሕርያቆስ ጸጋዬ በበኩላቸው፤ የገና በዓልን ሃይማኖታዊ ይዘቱን በጠበቀ መንገድ ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል።

ባለፉት ዓመታት ተቀዛቅዞ የነበረውን የገና በዓልን ዘንድሮ በተሻለ ሁኔታ ለማክበር እየተሰራ እንደሆነ ገልፀዋል።

ከወጣቶች፤ ከምዕመናን፣ ከሽማግሌዎች እንዲሁም ከካህናትና የእድር መሪዎች ጋር፤ በእንግዳ አቀባበል፣ ቅርሶችን በማስጎብኘት እንዲሁም ታዳሚውን ማስተናገድ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ተወያይተናል ብለዋል።

የከተማዋ ህዝብም የዘንድሮውን የገና በዓል የበለጠ አጉልቶ ለማሳየት እንግዶችን በልዩ ድምቀት ለመቀበል መዘጋጀት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የላሊበላ ከተማ ነዋሪ አቶ አያሌው ተስፋ በበኩላቸው እንዳሉት፤ የከተማው የንግድ እንቅስቃሴ በተለያዩ ምክንያቶች ተቀዛቅዞ መቆየቱን አስታውሰዋል።

እንግዶችን በመቀበል በዓሉን በድምቀት ለማክበር እንዲቻልም ከነዋሪዎች ጋር በመሆን ከአካባቢ ውበትና ጽዳት ጀምሮ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም