በላሊበላ ከተማ ህዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በላሊበላ ከተማ ህዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 3/2017(ኢዜአ)፦ በላሊበላ ከተማ ሰላምን በጋራ በማፅናት የተጀመሩ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የሚጠይቅ ህዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ እየተካሄደ ነው።
በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች ተከስተው በነበሩ የጸጥታ ችግሮች በተለይም እንደ ላሊበላ ያሉ ኢኮኖሚያቸውን በቱሪዝም ዘርፍ ጥገኛ ያደረጉ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች ቀዳሚ የጉዳቱ ሰለባ አድርገዋል።
የችግሩ ገፈት ቀማሽ የሆኑት የላሊበላ እና አካባቢው ነዋሪዎችም ‘ግጭት ይቁም፤ ሰላም ይስፈን’ የሚል መፈክር ይዘው ሰላማዊ ሰልፍ ወጥተዋል።
በሰላማዊ ሰልፉ በመንግሥት ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን እየተደረገ ያለውን ጥረት በመደገፍ ግጭትና ጦርነት ይብቃን የሚል ድምፃቸውን አሰምተዋል።
ከመንግስት ጎን በመቆም ሰላምን በጋራ በማፅናት የተጀመሩ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በመጠየቅም አጋርነታቸውን አሳይተዋል።
በሰላማዊ ሰልፉ “ሠላም ለሁሉም ሁሉም ለሠላም፤ ላሊበላ ከተማ ዘላቂ ሰላምን ትሻለች ለዚህም በቁርጠኝነት እንሰራለን” የሚሉ መልዕክቶችን አስተጋብተዋል።
የትኛውም አለመግባባት በጦርነት ሳይሆን በውይይትና በንግግር ሊፈታ እንደሚገባውም እንዲሁ።
“በተቀደሰው ስፍራ የተቀደሰ ሥራ እንጂ ግጭት ሊኖር አይገባም” በማለት ለህዝብና ለሀገር ሲባል ችግሮች በንግግር ይፈቱ ሲሉም ጠይቀዋል።
“ሰላም የከተማችን እስትንፋስ ሰላም ነው፤ ሰላም ቱሪዝም ነው” ሲሉም ለሰላማቸው መመለስ በጋራ እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።