ቀጥታ፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የልማት ጥያቄዎቻችን መመለስ ጀምረዋል - የምስራቅ ባሌ ዞን ነዋሪዎች

ባሌ፤ ታህሳስ 3/2017(ኢዜአ)፦ የምስራቅ ባሌ ዞን ነዋሪዎች ለረጅም ዓመታት ሲያነሷቸው የነበሩ የልማት ጥያቄዎች ከቅርብ ዓመታት ወዲህ መመለስ መጀመራቸውን ተናገሩ።

የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች በምስራቅ ባሌ እና ባሌ ዞኖች የልማት ስራዎች ጉብኝት እያደረጉ ነው።

በጉብኝታቸውም በምስራቅ ባሌ ዞን ለገ ሂዳ ወረዳ በኩታ ገጠም የለማ ማሽላ፣ በሰዌና ወረዳ ለተለያየ አገልግሎት የሚውል መለስተኛ ግድብ እና ጨልጨል የመስኖ ልማት ፕሮጀክትን ተመልክተዋል።


 

በተመሳሳይ በባሌ ዞንም በሲናና ወረዳ በኩታ ገጠም የለማ የስንዴ ማሳን ጎብኝተዋል።

ጉብኝቱን ተከትለው አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የዞኑ ነዋሪዎች አካባቢው በርካታ የልማት ችግሮች የነበሩት መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለይም የመሠረተ ልማት ጥያቄን በተደጋጋሚ ሲያነሱ እንደነበር ገልጸዋል።

በዞኑ የዳዌ ቃቸን ወረዳ ነዋሪ አቶ መሐመድ ጦና ሮባ እንዳሉት በአካባቢው የመንገድ መሠረተ ልማት አለመኖር ለበርካታ ችግር ሲዳርጋቸው መቆየቱን ይናገራሉ።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተለይም ከለውጡ ወዲህ ግን መንገድን ጨምሮ የተለያዩ መሠረተ ልማት ዝርጋታዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል።


 

የተጀመሩ የልማት ስራዎች የሚበረታቱ መሆኑን የጠቀሱት ነዋሪው፤ በተለይም ለግብርና ልማት ግብዓት ማቅረቢያ እና ለምርቶቻቸው የገበያ አማራጭ መዳረሻ መንገድና መሰል መሠረተ ልማቶች እንዲጠናከሩ ጠይቀዋል።

ሌላዋ የጊኒር ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ ሀዋ ሁሴን እንዳሉት ከለውጡ በኋላ መንግስት ችግራቸውን ለመፍታት እገዛ እያደረገ መሆኑ የሚያበረታታ መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም በተለያየ መልኩ ሲረዱ መቆየታቸውን የተናገሩት ወይዘሮ ሀዋ፤ አሁን ግን ወደ ግብርና ልማት መግባት የሚያስችላቸው የመስኖ ግድብ እንደተገነባላቸው አንስተዋል።

የምስራቅ ባሌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጃርሶ ቦሩ በበኩላቸው፤ ዞኑ በተለያየ ምክንያት በተገቢው ሳይለማ መቆየቱን ይናገራሉ።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ግን በግብርና ልማትና በሌሎች ዘርፎች ህዝቡን ተጠቃሚ ያደረጉ ስራዎች በመከናወን ላይ ናቸው ብለዋል።


 

የክልሉ ፕሬዚዳንት የልማት ፕሮጀክቶች አማካሪ አምባሳደር ሽፈራው ጃርሶ በበኩላቸው በክልሉ ዝናብ አጠር አካባቢዎች አነስተኛና መለስተኛ ግድቦችን በመገንባት ህዝብን ወደ ልማት የማስገባት ስራ እየተከናወነ መሆኑን አንስተዋል።

በተለይም "ፊና' በተሰኝ ፕሮጀክት በክልሉ ቆላማና ዝናብ አጠር አካባቢዎች በአነስተኛ ግድቦች ውሃን በመያዝ ውሃው ለመስኖ እና ለእንሰሳት መጠጥ እየዋለ መሆኑን ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ ትልቅ ተስፋ የተጣለበት እና የክልሉን እምቅ የልማት አቅም ለመጠቀም የሚያስችል መሆኑን በማከል።

 

በጉብኝቱ ወቅት አቶ ሽመልስ አብዲሳ እንዳሉት በምስራቅ ባሌ ዞን ያለውን አቅም ወደ ልማት ለመቀየር ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ነው።

በዞኑ ልማትን ሊያፋጥኑ የሚችሉ የመንገድ፣ የውሃ፣ የመብራት እና የቴሌኮም መሰረት ልማቶችን የማስፋፋት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ለአብነት በማንሳት።

ከዚህም ባለፈ የዞኑን የቱሪዝም ሀብት አሟጦ ለመጠቀም ተስፋ ሰጪ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው፤ በአካባቢው ያለውን የማዕድን ሀብትም በአግባቡ ለመጠቀም ትኩረት መደረጉን መናገራቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም