ቀጥታ፡

የዓለም የኤች አይ ቪ/ኤድስ ቀን በተለያዩ ዝግጅቶች በሻሸመኔ ከተማ እየተከበረ ነው

ሻሸመኔ፤ ታህሳስ 3/2017(ኢዜአ)፦ የዓለም የኤች አይ ቪ/ኤድስ ቀን በኦሮሚያ ክልል ደረጃ ዛሬ በሻሸመኔ ከተማ በእግር ጉዞና በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ነው።

በአሁኑ ወቅት ቀኑን በማስመልከት በተዘጋጀው የእግር ጉዞ ላይ የቀድሞው ተስፋ ጎህ ማህበር አባላት፣ የክልል እና የከተማ አስተዳደሩ አመራር አባላት፣ አባ ገዳዎች፣ ሀደ ሲንቄዎች፣ ተማሪዎች፣ ወጣቶች፣ የመንግስት ሰራተኞችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች እየተሳተፉ ነው።

የመርሀ ግብሩ ተሳታፊዎች በከተማዋ ዋና ዋና ጎዳናዎች ላይ በመዘዋወር የተለያዩ መፈክሮች እያሰሙ ይገኛሉ።


 

ከነዚህም "አንድም ሰው በኤች አይቪ/ኤድስ መያዝ የለበትም"፣ "ኤች አይ ቪ/ኤድስ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላልፍ እናስተምራለን"፣ "ከኤች አይ ቪ/ኤድስ ነፃ የሆነች ሀገር ማየት ህልማችን ነው" የሚሉና ሌሎችን ይጠቀሳሉ።

እንዲሁም  "ኤች አይ ቪ/ኤድስ የማህበረሰብ ጤና ችግር እንዳይሆን ኃላፊነታችንን ለመወጣት እንተጋለን" "ሰብዓዊ መብትን ያከበረ የኤች አይ ቪ/ኤድስ ህክምና አገልግሎት ለሁሉም ” በሚል መሪ-ቃል እየተከበረ ይገኛል።

ይህም ህብረተሰቡ ራሱን ከበሽታው እንዲጠብቅ፣ ግንዛቤ የማስፋት አገልግሎትን ተደራሽ እንዲሆን ያግዛል ተብሏል።

በቀጣይም ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ባሳተፈ የፖናል ውይይት የዓለም የኤች አይ ቪ/ኤድስ ቀን ታስቦ እንደሚውልም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም