ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ድርድር በስምምነት ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ ታህሳስ 3/2017(ኢዜአ)፦በቱርኪዬ ፕሬዚዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን አደራዳሪነት በአንካራ ለሶስተኛ ጊዜ የተካሄደው የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ድርድር ሁለቱንም አገራት በሚያግባባ ስምምነት ተጠናቋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ በቱርኪዬ ፕሬዝዳንት ጣይብ ኤርዶጋን ግብዣ ዛሬ ምሽት በአንካራ ውይይት አድርገዋል፡፡

ሁለቱ መሪዎች ውይይቱን ካደረጉ በኋላም በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

መሪዎቹ በመግለጫቸው ኢትዮጵያ በሶማሊያ የባሕር ዳርቻ በኩል ዘላቂና ደኅንነቱ የተጠበቀ የወደብ አማራጭ በምታገኝበት አማራጭ ላይ የቴክኒክ ውይይቶችን ለመጀመር መስማማታቸውን ገልፀዋል።


 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመግለጫቸው፤ ቱርኪዬ በአፍሪካ ቀንድ ሰላም እንዲሰፍን ለምታደርገው ከፍተኛ አስታዋፅኦ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያና የሶማሊያ ህዝቦች በቋንቋ፣ በባህል እና በደም የተሳሰሩ መሆናቸውንም ገልፀዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለጋራ ሰላምና ልማት ከሶማሊያ ጋር ለመስራት ቁርጠኛ መሆኗንም ተናግረዋል፡፡

ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ በበኩላቸው፤ የሶማሊያ መንግስት የኢትዮጵያ ወታደሮች ለሶማሊያ ሰላም የከፈሉትን መስዋዕትነት አይዘነጋም ሲሉ ገልፀዋል፡፡

ሁለቱ ሀገራት በቀጣይም ሰላምን ለማፅናት በሚያደረጉት ጥረት መንግስታቸው ቁርጠኛ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን በበኩላቸው፤ ሁለቱ ሃገራት የፈረሙት ሰነድ ትብብርን፣ የኢኮኖሚ እድገትን እና ብልጽግናን የሚያረጋግጥ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም