ስሑል ሽሬ በሊጉ ከወራጅ ቀጠና የወጣበትን ወሳኝ ሶስት ነጥብ አግኝቷል - ኢዜአ አማርኛ
ስሑል ሽሬ በሊጉ ከወራጅ ቀጠና የወጣበትን ወሳኝ ሶስት ነጥብ አግኝቷል
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 2 /2017(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ11ኛ ሳምንት ጨዋታ መርሃ ግብር ስሑል ሽሬ መቀሌ 70 እንደርታን 1 ለ 0 አሸንፏል።
ማምሻውን በድሬዳዋ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ አጥቂው ብርሃኑ አዳሙ በስምንተኛው ደቂቃ ያስቆጠራት ግብ ቡድኑን አሸናፊ አድርጋለች።
ውጤቱን ተከትሎ ስሑል ሽሬ በ11 ነጥብ ደረጃውን ከ17ኛ ደረጃ ወደ 14ኛ ከፍ በማድረግ ከወራጅ ቀጠና ወጥቷል። በውድድር ዓመቱም ሁለተኛ ድሉን አግኝቷል።
በሊጉ አራተኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው መቀሌ 70 እንደርታ በ10 ነጥብ ከነበረት 14ኛ ደረጃ ወደ 15ኛ ዝቅ በማለት ወራጅ ቀጠና ውስጥ ገብቷል።
ቀን ላይ በተደረገ የ11ኛ ሳምንት ጨዋታ የሊጉ መሪ መቻል እና ኢትዮጵያ መድን ያለ ምንም ግብ አቻ ተለያይተዋል።
ጨዋታዎቹን ተከትሎ የ11ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ተጠናቋል።
የሊጉ ውድድር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሱዳን ጋር በሚያደርገው የስምንተኛው የአፍሪካ አገራት እግር ኳስ ሻምፒዮና (ቻን) የደርሶ መልስ የማጣሪያ ጨዋታ ምክንያት እንደሚቋረጥ ከሊጉ አክሲዮን ማህበር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ሊጉ ከሁለት ሳምንታት ቆይታ በኋላ በድጋሚ ወደ ውድድር ይመለሳል።