በሀላባ ዞን ውጤታማ የለውጥ ሥራዎችን አጠናክሮ በማስቀጠል የላቀ እመርታ ለማስመዝገብ መስራት ይገባል - አቶ አህመድ ሽዴ - ኢዜአ አማርኛ
በሀላባ ዞን ውጤታማ የለውጥ ሥራዎችን አጠናክሮ በማስቀጠል የላቀ እመርታ ለማስመዝገብ መስራት ይገባል - አቶ አህመድ ሽዴ

ሀላባ፤ ታህሳስ 2/2017(ኢዜአ)፦ በሀላባ ዞን አበረታች ውጤት የተመዘገበባቸውን የለውጥ ሥራዎች አጠናክሮ በማስቀጠል የላቀ እመርታ ለማስመዝገብ ተግቶ መስራት እንደሚገባ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ተናገሩ።
በሚኒስትሩ የተመራ ቡድን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሀላባ ዞን እየተከናወኑ ያሉ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን ጎብኝቷል።
አቶ አህመድ ሽዴ በእዚህ ወቅት እንደገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የሰጡትን አመራር ተከትሎ የፌዴራል ከፍተኛ አመራሮች በተለያዩ ክልሎች የሱፐርቪዥን ሥራ እያከናወኑ ነው።
በአዲስ መልክ በተደራጀው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልልም የአገልግሎት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የሚያግዙ ቢሮዎች ግንባታና ሌሎች ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።
በጉብኝቱ በሀላባ ዞን በአርሶ አደሩና በግል ባለሀብቱ የሚከናወኑ የግብርና ልማት ሥራዎችን መመልከታቸውን ጠቁመው፣ በክልሉ ያለውን ውስን ሀብት ለመጠቀም የሚደረገው ጥረት መጠናከር አለበት ብለዋል።
የመንግስት ሠራተኛውን ጨምሮ ሁሉም ማህበረሰብ በሌማት ትሩፋት መርሃ-ግብር በዶሮ እርባታ እና በእንስሳት ተዋፅኦ መሳተፉ ገበያን ለማረጋጋት የሚሰሩ ሥራዎችን ጭምር እያገዘ መሆኑን ገልጸዋል።
በዞኑ የአርቶ ፍል ወሃ ስፍራን በማልማት ለቱሪዝም መዳረሻነት ለማዋል እየተከናወነ ያለው ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
በቁሊቶ ከተማ በማህበረሰብ ተሳትፎ እየተከናወነ ያለው የስታዲየም ግንባታ፣ የኮሪደር እና ሌሎች የልማት ሥራዎች አበረታች መሆናቸውን ተናግረዋል።
በመንግሥት የሚወርዱ ሁሉን አቀፍ የልማት አቅጣጫዎችን ፈጥኖ ተግባራዊ በማድረግ የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመረው ሥራ ይበል የሚያሰኝ ነው ብለዋል።
በአካባቢው ያሉ ሀብቶችን በአግባቡ አልምቶ መጠቀም ከተቻለ ተጨባጭ ለውጥ ማስመዝገብ እንደሚቻል በጉብኝቱ ወቅት መረዳታቸውንም አቶ አህመድ ተናግረዋል።
በመርሃ-ግብሩ ላይ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመሰረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የመንገድ ልማትና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ መሐመድ ኑርዬ(ዶ/ር)፣ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ልዩ አማካሪ አቶ ንጉሴ አስረስ እንዲሁም የሀላባ ዞን ከፍተኛ አመራሮች ተሳትፈዋል።