በሦስት ክልሎች በዘላቂ ሠላም ግንባታ የሚሰራ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 2/2017(ኢዜአ)፦ በመነጋገር ችግሮችን የመፍታት ነባር እሴቶችን በማጠናከር ዘላቂ ሠላም ማረጋገጥ እንደሚገባ የሠላም ሚኒስቴር አስገነዘበ።

ወርልድ ቪዥን በአማራ፣ በትግራይ እና በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልሎች ተግባራዊ የሚሆን በግጭት አፈታትና የሠላም ግንባታ ፕሮጀክት ዛሬ በአዲስ አበባ ይፋ አድርጓል።


 

በፕሮጀክቱ ይፋዊ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የሰላም ሚኒስትር ዴዔታ ከይረዲን ተዘራ(ዶ/ር)፤ ባደረጉት ንግግር ማናቸውንም ሀገራዊ ችግሮች በውይይት መፍታት የሁሉም ነገር ቁልፍ መፍትሄ መሆኑን አንስተዋል።

በዚህ ረገድ መንግስት ጽኑ አቋም ይዞ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረውን ጦርነት በውይይት ለመፍታት የነበረውን ቁርጠኝነት አስታውሰዋል።

ከኦሮሚያ ክልል የታጠቁ አካላት የሰላም አማራጭን ተቀብለው እጃቸውን ለሰላም መዘርጋታቸው ጥሩ ጀምር መሆኑን ገልጸው በሌሎች አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ የታጠቁ አካላትም ተመሳሳይ አማራጭ ሊከተሉ ይገባል ብለዋል።

ዛሬ ይፋ የሆነው ፕሮጀክት ለሰላም ግንባታ ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ፤ በበይነ-መረብ ባስተላለፉት መልእክት ከምንም በላይ ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት ሁሉም ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

በክልሉ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት በሚደረገው ጥረት ጊዜያዊ አስተዳደሩ ከምን ጊዜውም በላይ በቁርጠኝነት የሚሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የአማራ ክልል የገንዘብ ቢሮ ኃላፊ እና የክልሉ ፕሬዝዳንት ተወካይ ጥላሁን መሃሪ (ዶ/ር)፤ የክልሉ መንግስት ለሰላማዊ ንግግር ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።

የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የፋይናንስ ቢሮ ኃላፊና የፕሬዝዳንቱ ተወካይ ዚያድ አብዱላሂ በበኩላቸው፤ በክልሉ ያለውን ሰላም ዘላቂነት ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በአውሮፓ ኅብረት የሚደገፈው ይኸው ፕሮጀከት ለማስፈፀሚያ የሚውል 2 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ ከኅብረቱ ተደርጓል።

በኢትዮጵያ የወርልድ ቪዥን ዳይሬክተር ካርሜን ቲል፤ ፕሮጀክቱ የ18 ወራት ቆይታ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡

ዋና ዓላማውም የሠላም ግንባታ ሥራውን በማገዝ በክልሎች መካከል የውይይት ባህል እንዲጎለበት ማድረግ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም