የኢጋድ የህጻናት ረቂቅ ፖሊሲ ማዕቀፍ በቀጣናው የህጻናት መብትን በትብብር ለማስጠበቅ ያግዛል - ኢዜአ አማርኛ
የኢጋድ የህጻናት ረቂቅ ፖሊሲ ማዕቀፍ በቀጣናው የህጻናት መብትን በትብብር ለማስጠበቅ ያግዛል
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 2/2017(ኢዜአ)፦ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን(ኢጋድ) የህጻናት ረቂቅ ፖሊሲ ማዕቀፍ በቀጣናው የህጻናት መብትን በትብብር ለማስጠበቅ እንደሚያግዝ ተገለጸ።
በረቂቅ ፖሊሲ ማዕቀፍ ላይ የቴክኒክ ሙያተኞች ኮንፍረንስ በአዲስ አበባ በመካሔድ ላይ ይገኛል።
ፖሊሲው በህጻናት ላይ የሚደረግ መገለል፣ ጉልበት ብዝበዛና ሌሎች በህጻናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከልና ምላሽ ለመስጠት ተግባራዊ የሚደረጉ እቅዶችን አስቀምጧል።
የኢጋድ የወቅቱ ሊቀመንበር የጅቡቲ ፕሬዝዳንት ተወካይ ፎዚአ አሊ ኦስማን በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት ኢጋድ በአባል ሀገራቱ የሚገኙ የህጻናትን መብት ለማስጠበቅ እየሰራ ይገኛል።
በተመሳሳይ ህጻናት መብታቸውን በማወቅ ጠያቂ ሆነው እንዲያድጉ የህጻናት ፓርላማን ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑንና ፖሊሲው በትብብር ለመስራት ያለውን እድል ያሰፋል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሒክማ ከይረዲን በበኩላቸው ፖሊሲው በህጻናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለማስቀረት በትብብር ለመስራት እንደሚያገለግል ገልጸዋል።
በቀጣናው የሚኖሩ ህጻናት በድህነት፣ በጤና ተደራሽነት እጥረት፣ የግጭትና ስደት ገፈት ቀማሽ መሆናቸውን በመግለጽ ለችግሩ እልባት መስጠትና ምቹ ሁኔታን መፍጠር ለነገ የማይባል ስራ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ የህጻናት መብትና ጥቅሞችን ለማስጠበቅ እያከናወነች ያለውን ተግባር ከፖሊሲው ጋር በማቀናጀት ከአባል ሀገራት ጋር በትብብር ለመስራት ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል።
የኡጋንዳ የስርዓተ-ጾታ፣ ሰራተኛና ማህበራዊ ልማት ሚኒስቴር የወጣቶችና ህጻናት ጉዳዮች ኮሚሽነር ጋቢራኖ ፍሬድ ፖሊሲው በህጻናት ላይ የሚደረገውን ኢንቨስትመንት ለመጨመር እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
በመድረኩ የተገኙ የኢትዮጵያና ሶማሊያ ህጻናት ተወካዮች ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ፖሊሲው የህጻናትን ሰብዓዊ መብቶች በማስጠበቅ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል ብለው እንደሚጠብቁ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ህጻናት ፓርላማ የአዲስ አበባ ተወካይ ኢክራም ሲራጅና የሶማሊያ ህጻናት ተወካይ ሱአዳ ሞሃመድ ሃሰን አባል ሀገራቱ ፖሊሲውን አጽድቀው በመተግበር የህጻናትን መብት ማስጠበቅ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
ፖሊሲው እየተካሄደ ባለው ውይይት በግብዓትነት የሚቀርቡ ሃሳቦችን በማካተት ታህሳስ 4 ቀን 2017 ዓ.ም በሚደረገው የኢጋድ የሚኒስትሮች ስብሰባ ይጸድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተገልጿል።