በኦሮሚያ ክልል አዲሱ የቀበሌ አደረጃጀት የልማት መርሃ-ግብሮችን በቀበሌ ደረጃ ለማድረስ አቅም የሚፈጥር ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል አዲሱ የቀበሌ አደረጃጀት የልማት መርሃ-ግብሮችን በቀበሌ ደረጃ ለማድረስ አቅም የሚፈጥር ነው
መቱ፤ ታህሳስ 2/2017(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል አዲሱ የቀበሌ አደረጃጀት እንደመንግስት የተቀረጹት የልማት መርሃ ግብሮችን በቀበሌ ደረጃ ለማድረስና የሕዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አቅም እንደሚፈጥር በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቤልጂጌ(ዶ/ር) ገለፁ።
በዋና ተጠሪ ሚኒስትሩ የተመራ ቡድን በኢሉባቦር ዞን ሀሉ ወረዳ በአቢዩ ኪዳነ ምሕረት ቀበሌ በአዲሱ አደረጃጀት እየተከናወነ የሚገኘውን አጠቃላይ ስራ ተመልክቷል።
አደረጃጀቱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ብሎም በታችኛው አደረጃጀት ያለውን የሰው እና የተፈጥሮ ሀብት ለዜጎች ጥቅምና ለሀገር ልማት ለማዋል ትልቅ መሳሪያ እንደሆነም ተናግረዋል።
በአደረጃጀቱ የተጀመረው ስራ መልካም መሆኑን ከሕብረተሰቡ ግብረ መልስ ማወቅ መቻሉን ያነሱት ዋና ተጠሪ ሚኒስትሩ፤ በክልሉ ወደ ስራ የገባው አደረጃጀት ወደ ፊት ተገምግሞና ልምድም ተቀምሮበት ወደ ሌሎች ክልሎች እንዲስፋፋ የሚሰራ ይሆናል ብለዋል።
በኢሉባቦር ዞን 13 ወረዳዎች በሚገኙ 287 ቀበሌዎች በአዲሱ አደረጃጀት የተመደቡ ከ1 ሺህ 800 በላይ የቀበሌ አመራር አባላት ስራ የጀመሩ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ እንዳልካቸው ተፈሪ ናቸው።
በተራራቁ ቀበሌዎች ተበታትኖ የሚገኘውን የሰው ኃይል አደራጅቶ ወደ ስራ በማስገባት ልማትንና ዕድገትን ለማረጋገጥ ቀበሌን ማዕከል አድርጎ የሚሰራ መዋቅር መሆኑንም አመልክተዋል።
አስተያየት የሰጡ የሀሉ ወረዳ የአቢዩ ኪዳነ ምሕረት ቀበሌ ነዋሪዎች አዲሱ የቀበሌ አደረጃጀት አገልግሎት ለማግኘት ይሄዱ የነበረውን ረዥም ርቀት እንዳቃለለላቸው ገልጸዋል።