ሴቶችን በሰላምና ፀጥታ ጉዳይ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ በማድረግ ውጤታማ ስራ መስራት ይቻላል - ኢዜአ አማርኛ
ሴቶችን በሰላምና ፀጥታ ጉዳይ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ በማድረግ ውጤታማ ስራ መስራት ይቻላል
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 2/2017(ኢዜአ)፦ ሴቶችን በሰላምና ፀጥታ እንዲሁም በሽግግር ፍትህ ጉዳይ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ በማድረግ ውጤታማ ስራ መስራት እንደሚቻል የሴት አደረጃጀት ተወካዮች ገለፁ።
የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር ከጀርመን ኤምባሲ ጋር በመተባበር በሰላምና ፀጥና እንዲሁም በሽግግር ፍትህ ዙሪያ ከአፍሪካ የተለያዩ ሀገራት እንዲሁም ከሁሉም ክልሎች ከተውጣጡ የሴት አደረጃጀት ተወካዮች ጋር ውይይት አካሂዷል።
ጉባኤው ሴቶች ወደ አመራርነት እንዲመጡ እና አቅማቸውን እንዲያሳድጉ አስተዋጽኦ እንዳለው በዚሁ ወቅት ተገልጿል፡፡
ይህም በኢትዮጵያም ሆነ አጠቃላይ በቀጣናው መረጋጋትን ለመፍጠር እንዲሁም ችግርን የሚቋቋም ስርዓት ለመዘርጋት አወንታዊ አስተዋጽኦ ያለው ነው ተብሏል።
ከትግራይ ክልል የመጡት ወይዘሮ መብራት በየነ እንደገለጹት ሴቶች ዘላቂ ሰላምን ከማስፈን አኳያ ያላቸው ሚና ከፍተኛ ነው።
ሁሉን አቀፍና ዘላቂ ልማት እንዲሁም ሰብአዊ መብቶችን ለማስጠበቅ የስርአተ ፃታ እኩልነትን በማረጋገጥ ውጤታማ ማድረግ እንደሚቻልም ነው የጠቀሱት።
ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመጡት ወይዘሮ ሃይማኖት ታደሰም በተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋሉ ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሴቶች ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ነው የጠቀሱት።
የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያዎች ሴቶች ማህበር ዳይሬክተር ሌንሳ ብየና በዚሁ ወቅት እንዳሉት በአለማችን በተለያዩ አጋጣሚዎች በሚፈጠሩ ግጭቶች ዋነኛ ተጎጂዎች ሴቶች ናቸው።
የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታትም ሆነ ከግጭት ነፃ የሆነች አለም ለመፍጠር ሴቶችን በሰላምና ፀጥታ እንዲሁም በሽግግር ፍትህ ላይ ግንባር ቀደም ተሳታፊ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።
መድረኩ የአፍሪካ ሀገራት ሴቶች በሰላምና ደህንነት ዙሪያ ስላላቸው ተሳትፎ እና ምርጥ ተሞክሮ የልምድ ልውውጥ ለማድረግ እንደሚያግዝም ነው ዳይሬክተሯ የጠቆሙት።
በጀርመን ኤምባሲ የሴቶች የውጭ ፖሊሲ ዳይሬክተር ጌሳ ብራውትጋም በበኩላቸው ሴቶች ምን መስራት እንዳለባቸው ብቻ ሳይሆን እንዴት መስራት እንዳለባቸው ያውቃሉ ብለዋል፡፡
በዚህም ተፈጥሮ በቸራቸው ጥበብ በመጠቀም በርካታ ነገሮችን ማስተካከል እንደሚችሉ ጠቅሰዋል።
እንደ ጀርመን ባሉ ሀገራትም ሴቶች በሰላምና ፀጥታ ጉዳይ ያላቸው ተሳትፎ አነስተኛ መሆኑ በመጥቀስ።