የዲጂታል ዘርፉ ለዜጎች የስራ እድል ፈጠራ የሚኖረውን ጠቀሜታ ለማሳደግ ይሰራል - አቶ ሰለሞን ሶካ - ኢዜአ አማርኛ
የዲጂታል ዘርፉ ለዜጎች የስራ እድል ፈጠራ የሚኖረውን ጠቀሜታ ለማሳደግ ይሰራል - አቶ ሰለሞን ሶካ
አዲስ አበባ፤ ታኅሳስ 2/2017(ኢዜአ)፦ የስራና ክህሎት ሚኒስቴር የዲጂታል ዘርፉ ለዜጎች የስራ እድል ፈጠራ የሚኖረውን ጠቀሜታ ወደ ላቀ ደረጃ ከፍ ለማድረግ ከዘርፉ ተዋናዮችና አጋር አካላት ጋር በቅርበት የሚሰራቸውን ስራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ።
የጊግ ኢኮኖሚ ዘርፍ ለሀገር ሁለንተናዊ እድገት ብሎም ለዜጎች የስራ እድል ከመፍጠር አኳያ መልካም እድሎች እንደሚያመጣ ይታወቃል፡፡
ጊግ ኢኮኖሚ ወይም የቁርጥ ስራ አገልግሎት ሰጪንና ተቀባይን የሚያገናኙ ፕላት ፎርሞች ናቸው።
ይህንኑ ጉዳይ በተመለከተ ለመምከር ብሎም ዘርፉን ለማስተዋወቅ ዓላማ ያለው የታለንት ክላውድ ጉባኤ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ዛሬ ተካሂዷል።
የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሰለሞን ሶካ በዚህ ወቅት እንደገለጹት መንግስት የሀገሪቱን ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ እድገት ለማፋጠን እየሰራ ይገኛል፡፡
በዚህም መንግስት የሀገሪቱን ተወዳዳሪነት ማጎልበት የሚያስችሉ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ቀርጾ በመተግበር ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
የቴክኖሎጂ አቅምን በአግባቡ ስራ ላይ በማዋል ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ተግባራዊ የተደረገው የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ለዚህ ተጠቃሽ መሆኑን አንስተዋል።
ሚኒስቴሩ የዲጂታል ዘርፉ ለዜጎች የስራ እድል ፈጠራ የሚኖረውን ጠቀሜታ ለማሳደግ ከዘርፉ ተዋናዮች እና አጋር አካላት ጋር እየሰራ እንደሚገኝ በመጥቀስ ይህንኑ ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
ለዚህም ማሳያ ሚኒስቴሩ በበጀት ዓመቱ ባለፉት ሶስት ወራት በብቁ የስራ ገበያ መረጃ ስርአት ከመጡ 86 ሺህ የሪሞት ጆብስ የስራ እድሎች መካከል ከ26 ሺህ በላይ ዜጎች የስራ እድሉ ተጠቃሚ መሆናቸውን አክለዋል።
ቴክኖሎጂን በመጠቀም የስራ እድሎችን እውን ለማድረግ የተለያዩ የዲጂታል ፕላት ፎርሞች ትልቅ አቅም የሚፈጥሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ከዚህም ውስጥ ጊግ ኢኮኖሚ ወይም የቁርጥ ስራ አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ፕላት ፎርሙ ዜጎች የዲጂታል ውጤቶችን በመጠቀም የስራ እድሎችን በመወዳደር ለማግኘት ያላቸውን እድል የሚያሰፋ መሆኑን አክለዋል።
የገበያ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ኦፊሰር አማዱ ዳፌ በበኩላቸው የአፍሪካ የጊግ ኢኮኖሚ ለዜጎች መልካም የስራ እድልን ይዞ የሚመጣ መሆኑን ተናግረዋል።
የተባበሩት መንግስታት የንግድ ቀጣና የኢትዮጵያ አስተባባሪ ሳሙኤል ፈቃደ ጊግ ኢኮኖሚ ወጣቶች ያላቸውን ጊዜ፣ ዕውቀት እና ክህሎት አሟጠው በመጠቀም ራሳቸውን በኢኮኖሚ የሚያሳድጉበት እና ህይወታቸውን መለወጥ የሚችሉበትን ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል።
ጊግ ኢኮኖሚ በሀገር ውስጥና በአለም አቀፍ ደረጃ ያሉ አማራጮችን ለመጠቀም የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን በመረዳት ዘርፉን የመጠቀም ልምዳችንን ልናጎለብት ይገባል ብለዋል።
በውይይቱ የተሳተፉት ወጣት ሞናሊዛ ሀይሌ እና እዩኤል ከፍያለው በበኩላቸው የጊግ ኢኮኖሚ ወጣቶች ያላቸውን የፈጠራ አቅም እና ችሎታ በመጠቀም የተሻለ ስራ መስራት የሚችሉበትን አቅም ለማሳደግ የሚያግዝ ነው ብለዋል።
በተለይም ወጣቶች የስራ እድል የማግኘት እድላቸውን የሚያጎለብት በመሆኑ ፕላት ፎርሙን የመጠቀም ባህል ማጎልበት አለብን በማለት ለዘርፉም እድገት የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላቶች ድጋፍና ርብርብ ወሳኝ ነው ብለዋል።
የዛሬውን ጉባኤ ያዘጋጁት የስራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ ገበያ፣ የተባበሩት መንግስታት ዓለም አቀፍ የንግድ ማዕከል እና የኔዘርላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ናቸው።