ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የደንበኞችን ቅሬታ በፍጥነት ለመፍታት የጀመረውን ሪፎርም ማጠናከር አለበት - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 2/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የደንበኞችን ቅሬታ በፍጥነት ለመፍታት የጀመረውን ሪፎርምና የዲጂታላይዜሽን አሰራር ማጠናከር እንዳለበት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትን የጥሪ ማዕከልና የመረጃ ቋት ጎብኝተዋል።

ጉብኝታቸውን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያም መንግሥት አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል ሪፎርም እያካሄደ መሆኑን ጠቅሰው የኤሌክትሪክ አገልግሎት ሪፎርም የዚሁ አካል ነው ብለዋል።


 

የኤሌክትሪክ አገልግሎቱ በከተማ የኮሪደር ልማት የኃይል መቆራረጥ እንዳይኖር በአፋጣኝና በተቀናጀ መንገድ የመስመር መልሶ ዝርጋታ ላይ እየተገበረ ያለው ስራ የሚደነቅ ነው ብለዋል።

አገልግሎቱ በህብረተሰቡ የሚነሱበትን ቅሬታዎች በፍጥነት ለመፍታት የጀመራቸው የዲጂታላይዜሽንና መሰል ሪፎርሞች የሚበረታቱ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።

የሚመረተው የኤሌክትሪክ ኃይል ለህብረተሰቡ በአግባቡ እንዲደርስ ማድረግና ብክነትን ለመቀነስ ትኩረት ያስፈልጋል ነው ያሉት።

የቆጣሪ እና የትራንስፎርመር ምርትን በአግባቡ ለህብረተሰቡ ተደራሽ ማድረግና የአቅርቦት መጠኑንም መጨመር እንደሚገባ አሳስበዋል።


 

መንግሥት የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽነትን ከከተማ እስከ ገጠር ለማስፋፋት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው አገልግሎቱም በአንድ በኩል ትርፋማ መሆን በሌላ በኩል ደግሞ ፈጣን አገልግሎት መስጠት ይጠበቅበታል ብለዋል።

በተለይም ከሌብነት የጸዳና ግልፅ አገልግሎት ለመስጠት የሰው ኃይልና የቴክኖሎጂ ልህቀት ዋነኛ ትኩረቱ እንዲሆን አሳስበዋል።

መብራት የደም ሥር ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በህብረተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ፍላጎት እንዳለም አንስተዋል።

ለዚህ ፍላጎት ፈጣን ምላሽ መስጠት ተቋማዊ ሃላፊነት መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ላይ ከፍተኛ ስርቆትና ውድመት እንደሚፈጸምም ጨምረው ተናግረዋል።

በዚህም ዋነኛ ተጎጂዎቹ ሀገርና ዜጎች በመሆናቸው ህብረተሰቡ በየአካባቢው ያሉ መሰረተ ልማቶችን መጠበቅ እንዳለበት አፅንኦት ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም