ሙስናን የሚፀየፍና በስነ-ምግባር የታነጸ ትውልድ ለመፍጠር የተቀናጀ ርብርብ ያስፈልጋል - ኢዜአ አማርኛ
ሙስናን የሚፀየፍና በስነ-ምግባር የታነጸ ትውልድ ለመፍጠር የተቀናጀ ርብርብ ያስፈልጋል
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 2/2017(ኢዜአ)፦ ሙስናን የሚፀየፍና በስነ-ምግባር የታነጸ ትውልድ ለመፍጠር የተቀናጀ ርብርብ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን የ21ኛው ዓለም አቀፍ የፀረ-ሙስና ቀን የማጠቃለያ መድረክ ተሳታፊዎች ገለጹ፡፡
ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ በተገኙበት 21ኛው ዓለም አቀፍ የፀረ-ሙስና ቀን የማጠቃለያ መድረክ በአድዋ መታሰቢያ ተካሂዷል፡፡
በመድረኩ ላይ የተገኙት በስነ-ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን የስነ-ምግባር ግንባታ እና ሙስናን መከላከል መሪ ስራ አስፈጻሚ ሐረጎት አብርሀ ወጣቶች የተጠያቂነት ስሜት እንዲያዳብሩ መስራት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህ ባለፈ ወጣቶች የተጠያቂነት ስሜትንና የእኔነትን ባህል እንዲያዳበሩ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
መምህር ዳንኤል ሰይፈሚካኤል በበኩላቸው መንግስት እና የሃይማኖት ተቋማት አብረው ሊሰሩባቸው ከሚችሉ ጉዳዮች መካከል ትልቁ ስነ-ምግባር መሆኑን ተናግረዋል።
ከሃይማኖት ተቋማት ጋር በመተባበርና የማስተማሪያ ስልቶችን በመንደፍ ስነ-ምግባርን ከቃላት አጠቃቀም አንስቶ እንዲረዱ ለማስቻል በትብብር መስራት እንደሚገባ አመላክተዋል።
መልካም ነገሮችን ማስቀጠል መልካም ያልሆኑ ተግባራትን ደግሞ ማረም እንደሚገባ የገለጹት ደግሞ ቀሲስ መዝገቡ ካሳ ናቸው።
ስነ-ምግባርን የሚያጎለብቱ ስራዎችን በስፋት መስራት እና ሙስናን የሚያበረታቱ ነገሮችን ማረም እና ማስተካከል እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የትምህርት እና ስልጠና ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ ሙክታር ሁሴንም ሙስናን የሚጠየፍና በስነ ምግባር የታነጸ ዜጋ ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት መገናኛ ብዙሃን ጉልህ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል።
በዘርፉ የተጀመሩ ስራዎች ውስንነት እንዳለባቸው ገልጸው በቀጣይ የመገናኛ ብዙሃን ዋና የትኩረት አቅጣጫ መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል።