በሦስት ክልሎች ተግባራዊ የሚሆን የሠላም ግንባታ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ - ኢዜአ አማርኛ
በሦስት ክልሎች ተግባራዊ የሚሆን የሠላም ግንባታ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ፤ ታኅሳስ 2/2017 (ኢዜአ)፦ በመነጋገር ችግሮችን የመፍታት ነባር እሴቶችን በማጠናከር ዘላቂ ሠላም ማረጋገጥ እንደሚገባ የሠላም ሚኒስቴር አስገነዘበ።
ወርልድ ቪዥን በአማራ፣ በትግራይና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ተግባራዊ የሚሆን የሠላም ግንባታ ፕሮጀክት ዛሬ በአዲስ አበባ ይፋ አድርጓል።
ፕሮጀክቱ ወጣቶች የሠላም ግንባታን ባህል አድርገው እንዲሰሩ በማብቃትና በሠላም ግንባታ የተሻለ አቅም እንዲኖራቸው የሚያስችል መሆኑን ተገልጿል።
በአውሮፓ ኅብረት የሚደገፈው ይኸው ፕሮጀከት ለማስፈፀሚያ የሚውል ሁለት ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ ከኅብረቱ ተደርጓል።
የሠላም ሚኒስቴር የሠላም ግንባታና ብሔራዊ መግባባት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ሠላም የሁሉም ዜጋ ጉዳይ በመሆኑ ለዘላቂነቱ የጋራ ርብርብ ያስፈልጋል።
መንግሥት በአንዳንድ የአገሪቷ አካባቢዎች የተከሰቱ የሠላም እጦቶችን ለመቅረፍ በንግግር የመፍታት ቁርጠኛ አቋም በመያዝ ችግሮችን በሠላማዊ መንገድ እየፈታ እንደሚገኝ ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።
ከወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ በመነጋገር ችግሮችን የመፍታት ነባር እሴቶችን በማጎልበት የሠላም እጦት በሚስተዋልባቸው አካባቢዎች ሠላምን ለመገንባት እየሰራ ያለውን ሥራ አመስግነዋል።
ለፕሮጀክቱ ውጤታማነት የሠላም ሚኒስቴር አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።