በባሌ ዞን በግብርናው ዘርፍ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ሥራዎች በተሞክሮነት የሚወሰዱ ናቸው - ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ - ኢዜአ አማርኛ
በባሌ ዞን በግብርናው ዘርፍ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ሥራዎች በተሞክሮነት የሚወሰዱ ናቸው - ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ
ሮቤ፤ ታህሳስ 2/2017(ኢዜአ)፦ በባሌ ዞን በግብርናው ዘርፍ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ሥራዎች በተሞክሮነት የሚወሰዱ መሆናቸውን የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገለጹ።
የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በባሌ ዞን በአጋርፋና ሲናና ወረዳዎች እየተከናወኑ የሚገኙ የልማትና የግብርና ኢንሼቲቮችን ጎብኝተዋል።
ከተመለከቷቸው ሥራዎች መካከል በመኽሩ ወቅት በኩታ ገጠም አሰራር እየለማ የሚገኘውን የስንዴ ልማት፣ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት እና የሌማት ትሩፋት ሥራዎች ይገኙበታል።
እንዲሁም የሲኮ መንዶ የገበሬዎች ህብረት ሥራ ዩኒየን የግብርና ሜካናይዜሽን ማዕከልም የጉብኝቱ አካል ነው።
ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት በዞኑ በግብርናው ዘርፍ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ሥራዎች በተሞክሮነት የሚወሰዱ ናቸው።
በተለይም አርሶ አደሩ የተሻሻሉ የግብርና አሰራሮችን ተግባራዊ በማድረግ በኩታ ገጠም ልማት እያከናወነ የሚገኘውን ጥረት በማሳያነት አቅርቧል።
በየአካባቢው እየተካሄዱ ያሉ ልማቶች ተጨባጭ መሆናቸውን በዞኑ የተመለከቱት ይህንኑ ጥረት በተግባር ያመላከተና የሚደነቅ ነው ብለዋል።
ዞኑ በዘንድሮ የመኽር ወቅት ከ580 ሺህ ሄክታር በላይ በተለያዩ የሰብል ዘሮች መልማቱን የገለጹት ደግሞ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱልሐኪም አልዪ ናቸው።
ከዚህ ውስጥ ከ340 ሺህ የሚበልጥ መሬት በኩታ ገጠም የለማ ስንዴ ሲሆን፣ ከአጠቃላይ ልማቱም ከ25 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል ብለዋል።