ተቋሙ የአገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል የጀመረውን ሪፎርም እንዲያጠናክር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳሰቡ - ኢዜአ አማርኛ
ተቋሙ የአገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል የጀመረውን ሪፎርም እንዲያጠናክር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳሰቡ
አዲስ አበባ፤ ታኅሳስ 2/2017 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የአገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል እያደረገ ያለውን ሪፎርም አጠናክሮ እንዲቀጥል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ አሳሰቡ።
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የተመሩ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ሃላፊዎች በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በደንበኛ አገልግሎት መስጫና በጥሪ ማዕከል ዛሬ የመስክ ምልከታ አድርገዋል፡፡
በጉብኝቱ ወቅት ተቋሙ ለደንበኞቹ የሚሰጠውን አገልግሎት የተሻለ ለማድረግ እያከወናቸው የሚገኙ የሪፎርም ሥራዎችን ተመልክቷል፡፡
በዚሁ ጊዜ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተቋሙን የአገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል ተገቢ እና ጠቃሚ ሪፎርሞች በትኩረት እና በትጋት እንዲፈጸሙ አሳስበዋል።
የአገልግሎት አሰጣጥን ውጤታማ ማድረግ የመንግሥት ትኩረት በመሆኑ በዚህ ረገድ የተጀመሩት የሪፎርም ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
አገልግሎቱ በርካታ ደንበኞችን የማስተናገድ ዐቅሙን በማሳደግ እንግልትን ለመቀነስና ግልጽ የአሠራር ሥርዓትን ለመተግበር ባከናወናቸው ተግባራት ላይም ውይይት ተደርጓል።
በደንበኛ አገልግሎት መስጫ፣ በዳታ ሴንተር እና በጥሪ ማዕከል እየተተገበሩ በሚገኙ ሥራዎች፣ የኤሌክትሪክ ኃይልን በማቅረብ ተልዕኮ ሂደት የሚያጋጥሙ መሠረታዊ ተግዳሮቶችን በዘላቂነት ለመፍታት በሚያስችሉ ተግባራት ላይም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።