በክልሉ ለሚካሄደው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ስኬታማነት ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን ሚና መወጣት አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ለሚካሄደው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ስኬታማነት ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን ሚና መወጣት አለባቸው
አዳማ፤ ታህሳስ 2/2017(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል በቀጣዩ ሳምንት የሚካሄደው የአጀንዳ ማሰባሰብና የምክክር ተሳታፊዎች መረጣ ሂደት ስኬታማ እንዲሆን ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲወጡ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስገነዘበ።
በክልሉ በሚካሄደው የአጀንዳ ማሰባሰብና የምክክር ተሳታፊዎች መረጣ ሂደት የባለድርሻ አካላት ሚና ላይ ያተኮረ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪል ማህበራት፣ የወጣቶችና የሴቶች አደረጃጀቶች የተሳተፉበት መድረክ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ መላኩ ወልደማርያም በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የሀገራዊ ምክክሩ ዓላማ ችግር ውስጥ የቆየንባቸው ቁርሾዎችን ተመካክሮ መፍታት ነው።
በተለይም ለነበሩ አለመግባባቶችና ቁርሾዎች መፍትሔ መስጠት የምንችለው በምክክር ብቻ ነው ያሉት ኮሚሽነሩ፤ በክልሉ የሚካሄደው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት የተሳካ እንዲሆን ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን መወጣት አለባቸው ብለዋል።
አዲስ አበባና ድሬዳዋን ጨምሮ በበርካታ ክልሎች አጀንዳ የማሰባሰብ ሂደቱ መጠናቀቁን የገለፁት አቶ መላኩ፤ ኦሮሚያም ሰፊ ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበት በመሆኑ ለክልሉ ህዝብና ለአገር የሚበጁ አጀንዳዎችን የማሰባሰብ ሂደቱን ውጤታማ ማድረግ አለብን ነው ያሉት።
ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ህብረት ፓርቲ ሰብሳቢ አቶ ገብሩ በርሔ እንዳሉት በክልሉ የሀገራዊ ምክክሩን የተሳካ ለማድረግ ከሂደቱ ጀምሮ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ላይ ናቸው።
በተለይም ለክልሉም ሆነ ለኢትዮጵያ ምን ይበጃል? የሚለውን ከሂደቱ ጀምሮ የሐሳብ የበላይነት የተንፀባረቀበት ነው ብለዋል።
እንደፓርቲ ለሀገራችን የሚበጅ አጀንዳ ለማቅረብ ተዘጋጅተናል ያሉት አቶ ገብሩ፤ በዚህም አጀንዳ ይዘው የሚቀርቡ አምስት አካላት መምረጣቸውን ተናግረዋል።
ከሲቪል ማህበራት የመጡት መቶ አለቃ አሰፋ አጂቤ በበኩላቸው፤ ከመጪው ሰኞ ጀምሮ የሚካሄደው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ የነበሩብንና አሁንም ያሉብንን ችግሮች በውይይት የምንፈታበት መሆን አለበት ብለዋል።
በተለይም የነበሩ ቁርሾዎችን በምክክር ለመፍታት ማህበረሰቡ ትክክለኛውን አጀንዳ እንዲያቀርብ ማድረግ አለብን ነው ያሉት።
የኦሮሚያ ወጣቶች ፌዴሬሽን ተወካይ ወጣት አሪፊ ሃጂ ሙሐመድ በበኩሉ በሀገሪቱ በነበረና አሁን እየተከሰተ ባለው ችግር ቀዳሚ ተጎጂ ወጣቶች ናቸው ብሏል።
በሀገራዊ ምክክሩ የወጣቶችን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት ወሳኝነት ያላቸው አጀንዳዎችን አንስተው እንደሚመክሩበት አንስቷል።
በዚህም ወጣቱ በመጪው ሳምንት በክልሉ በሚካሄደው የአጀንዳ ማሰባሰብና የምክክር ተሳታፊዎች መረጣ ላይ በንቃት በመሳተፍና የወጣቱን አጀንዳ ለመስጠት መዘጋጀቱንም ገልጿል።