ትውልድን በሥነ-ምግባር በመቅረጽ የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ትውልድን በሥነ-ምግባር በመቅረጽ የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፤ ታኅሳስ 2/2017 (ኢዜአ)፦ትውልድን በሥነ-ምግባር በመቅረጽ የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልጽግና እንዲረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን የሥነ-ምግባር እና ፀረ-ሙስና ኮሚሽነር ሳሙኤል ኡርቃቶ (ዶ/ር) ገለጹ።
የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ በተገኙበት 21ኛው ዓለም አቀፍ የፀረ-ሙስና ቀን የማጠቃለያ መድረክ በአድዋ መታሰቢያ አዳራሽ ተካሂዷል፡፡
በመድረኩም ፕሬዝዳንቱን ጨምሮ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እውነቴ አለነ፣ የምክር ቤት አባላት፣ ሚኒስትሮች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
ኮሚሽነር ሳሙኤል በመድረኩ ላይ እንዳሉት ኮሚሽኑ በሥነ-ምግባር ግንባታና ሙስና በመከላከል ረገድ ጠንካራ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል።
ይሁን እንጂ ሕግን በማስከበር በኩል የተሰራው ሥራ ውስንነት የታየበት በመሆኑ በቀጣይ ተገቢው ትኩረት ተሰጥቶት ይሰራበታል ብለዋል።
ሙስና ትውልድን የሚገድልና አገር እንዳትበለጽግ የሚያደርግ ነው ያሉት ኮሚሽነሩ ይህን ከወዲሁ መግታት እንደሚገባ አስምረውበታል።
በመሆኑ ትውልድን በሥነ-ምግባር በመቅረጽ ለኢትዮጵያ ብልጽግና መሳካት ኮሚሽኑ በዚህ ላይ እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
እየተደረገ ያለው የፀረ-ሙስና ትግል አሁን ላይ ተስፋ ሰጭ መሆኑን ኮሚሽነሩ ጠቅሰው ትግሉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
ሙስናን የመከላከል ሥራ ለመንግሥት ብቻ የሚተው ባለመሆኑ ሁሉም የጋራ አጀንዳ ሊያደርገው እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
21ኛው ዓለም አቀፍ የፀረ-ሙስና ቀን “ወጣቶችን ያማከለ የፀረ-ሙስና ትግል የነገን ስብእና ይገነባል” በሚል መሪ ሀሳብ ተከብሯል።