ቀጥታ፡

የኤርፖርት እና ድንበር አስተዳደር ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም ስርዓት የትብብር ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ፤ታህሳስ 2/2017(ኢዜአ)፦ዘጠኝ ተቋማት የኤርፖርት እና ድንበር አስተዳደር ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም ስርዓት የትብብር ስምምነት ተፈራረሙ።

ስምምነቱን የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ በርሆ ሃሰን፣ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል ሲሳይ ቶላ፣ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግሥት ሃሚድ፣ የጉሙሩክ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ሙሉወርቅ ደረስ፣ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ዋና ስራ አስፈፃሚ ጌታቸው መንግስቴ፣ የኢትዮጵያ አርተፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ቢኒያም እንደሻው፣ የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው ናቸው የተፈራረሙት። 

ስምምነቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ያለውን ታላቅ ስምና ዝና ለማስቀጠል እንዲሁም የድንበር ደህንነትን ይበልጥ ለማሳደግ ያስችላል ተብሏል። 

ተቋማቱ የደረሱበት ስምምነት በቅንጅት እንዲሰሩ ብሎም መረጃዎችን እንዲለዋወጡ የሚያስችላቸው መሆኑም ተጠቁሟል። 

የስምምነቱ ዋነኛው ምክንያት የኢትዮጵያ አየር መንገድን ክብርና ዝና ማስቀጠል መሆኑ ተገልጿል።

የአየር መንገዱን አሰራሮች ማሳደግ ከስምምነቱ መሰረታዊ ምክንያቶች ውስጥ እንደሚካተት የተገለጸ ሲሆን ሂደቱ የተቋሙን ተወዳዳሪነት ይበልጥ እንደሚያሳድገው በመድረኩ ተነስቷል። 

ይህም አሰራሮችን በቴክኖሎጂ በማቀናጀት የመረጃ ልውውጡን ለማሳለጥ ያስችላል ተብሏል።

የአቪዬሽን ደህንነትን በቴክኖሎጂ በማስጠበቅ የመንገደኞችን ምቾትና የሀገርን ደህንነት ይበልጥ ለማረጋገጥም ስምምነቱ አጋዥ መሆኑም ተጠቅሷል። 

በኢትዮጵያ የሚገኙ የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በርካቶች እንዲጎበኟቸው ማስቻልም ሌላኛው የስምምነቱ ዓላማ መሆኑ ተገልጿል። 

እንዲሁም የድንበር አስተዳደር ቁጥጥርን ይበልጥ ለማሻሻል  እንደሚያግዝ ነው በዚሁ ወቅት የተገለጸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም