ቀጥታ፡

11ኛው ዙር አገር አቀፍ የጥራት ሽልማት መርሃ ግብር ታህሳስ 5 ይካሄዳል

አዲስ አበባ፤ታህሳስ 2/2017(ኢዜአ)፦11ኛው ዙር አገር አቀፍ የጥራት ሽልማት መርሃ ግብር ቅዳሜ ታህሳስ 5 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት አስታወቀ።

ድርጅቱ በየዓመቱ በኢትዮጵያ ውስጥ በማምረትና አገልግሎት በመስጠት ላይ የተሰማሩ ድርጅቶችን በተቋማዊ የጥራት ሥራ አመራር መለኪያ መሥፈርቶች በማወዳደር እውቅና እና ሽልማት እንደሚሰጥ ገልጿል።

ድርጅቱ 11ኛውን አገር አቀፍ የጥራት ሽልማት ስነ ስርዓት ታህሳስ 5 ቀን 2017 ዓ.ም በታላቁ ቤተ መንግሥት እንደሚያከናውን ለኢዜአ በላከው መረጃ አመልክቷል።

ሽልማቱ ዓለም አቀፍ የጥራት መስፈርትን ላሟሉ ተቋማት የሚሰጥ መሆኑ ተገልጿል።

ከመወዳደሪያ መስፈርቶቹ መካከል የሕዝብ አገልግሎት አሰጣጥ፣ የኃብት አጠቃቀም፣የአመራር ሰጪነት፣ የደንበኞች አያያዝ፣የሥራ አፈጻጸምና ሌሎችንም መስፈርቶች ተካተዋል።

በሽልማቱ ስነ ስርዓት የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት እና የድርጅቱ የበላይ ጠባቂ ታዬ አጽቀ ሥላሴ፣ከፍተኛ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች፣የኩባንያ ባለቤቶች እና ሥራ አስፈጻሚዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንደሚገኙ ድርጅቱ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም