ቀጥታ ስርጭት

በምሥራቅ ባሌ ዞን ያለውን የልማት አቅም አሟጦ ለመጠቀም የተጀመረው ጥረት ውጤታማ ነው - አቶ ሽመልስ አብዲሳ

ባሌ ፤ታህሳስ 02/ ቀን 2017 (ኢዜአ)፥በምሥራቅ ባሌ ዞን ያለውን የልማት አቅም አሟጦ ለመጠቀም የተጀመረው ጥረት ውጤታማ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ አስታወቁ።

የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ እና ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች በምሥራቅ ባሌ ዞን የልማት ስራዎችን እየጎበኙ ነው።

በዛሬው ጉብኝታቸው በዞኑ ለገ ሂዳ ወረዳ በአምስት ሺህ ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም የለማውን ማሽላ ሰብል ጎብኝተዋል።

በዚሁ ወቅት ፕሬዚዳንት ሽመልስ እንደገለጹት፤ የክልሉ መንግስት በዞኑ ያለውን የልማት አቅም ለይቶ ወደ ልማት ተገብቷል።

በዞኑ የረጅም ጊዜ የልማት እንቅፋት ሆኖ የቆየውን የመሠረተ ልማት ችግር ለመፍታት ሰፋፊ ስራዎች መጀመራቸውን በማከል።

በተለይም የመንገድ፣ የንፁህ መጠጥ ውሃ፣ የኤሌትሪክ ሃይል አቅርቦትና የቴሌኮም ችግሮችን ለመፍታት ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል።

በዚህም የመንገድ ችግር እየተፈታ መምጣቱን አንስተው፤ የውሃ ችግር ለመፍታትም የመስኖ ግድቦችን ጨምሮ የተለያዩ ጅምር ስራዎች እንዳሉ አስረድተዋል።

በዞኑ የሚገኙ የሶፍ ኡመር ዋሻና ሼክ ሁሴንን ጨምሮ ሌሎች የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎችን የማልማቱ ስራም ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል።

በተጨማሪም የዞኑን የማዕድን ሀብት በአግባቡ በማልማት የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በአጠቃላይ በዞኑ ያለውን እምቅ አቅም ወደ ልማት ለመቀየር የተጀመረው ጥረት ውጤት እያመጣ መሆኑን ፕሬዚዳንቱ አረጋግጠዋል።

የምስራቅ ባሌ ዞን ግብርና ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ዘላለም አለማየሁ በበኩላቸው፤ በዞኑ በመኸር እርሻ ከ500 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት መልማቱን ተናግረዋል።

ከዚህ ውስጥ አምስት ሺህ ሄክታር መሬት በማሽላ በኩታ ገጠም የለማ ሲሆን፤ ከዚህም 150 ሺህ ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

በልማቱ የተሳተፉ አርሶ አደሮችም ከዚህ ቀደም ምንም የግብርና ልማት የማይካሄድበት መሬት በማልማት ተጠቃሚ መሆን መጀመራቸውን ጠቁመዋል።

የስራ ሀላፊዎቹ ጉብኝታቸውን ቀጥለው በዞኑ ለተለያየ ጥቅም እንዲውል የተገነባውን መለስተኛ የውሃ ግድብ እየተመለከቱ ነው።

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም