በቀጣዮቹ ሶስት ወራት የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ማስተግበሪያ አዋጆች እንደሚጸድቁ ይጠበቃል -ሚኒስትር ሃና አርዓያሥላሴ - ኢዜአ አማርኛ
በቀጣዮቹ ሶስት ወራት የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ማስተግበሪያ አዋጆች እንደሚጸድቁ ይጠበቃል -ሚኒስትር ሃና አርዓያሥላሴ
አዲስ አበባ፤ታህሳስ 1/2017(ኢዜአ)፦በቀጣዮቹ ሶስት ወራት የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ማስተግበሪያ አዋጆች ጸድቀው ወደ ስራ እንዲገቡ ለማስቻል እየተሰራ መሆኑን የፍትህ ሚኒስትሯ ሃና አርዓያሥላሴ ገለጹ።
የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ባለፈው አመት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ፀድቆ በፖሊሲው ላይ የተካተቱ ዋና ዋና መርሆዎችን ለመተግበር በፍትህ ሚኒስቴር በኩል የተለያዩ ተግባራት ሲከናወኑ ቆይተዋል።
በዛሬው እለትም ሚኒስቴሩ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲን ለማስተግበር በተዘጋጁ ረቂቅ የህግ ማእቀፎች ዙሪያ ያዘጋጀው ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ በአዲስ አበባ አካሂዷል።
በመድረኩ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲን ለማስተግበር የተዘጋጁ ረቂቅ የህግ ማእቀፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
የፍትሕ ሚኒስትር ሃና አርዓያሥላሴ በዚሁ ወቅት፥ ፖሊሲውን ለመተግበር አስፈላጊ የሆኑ ተቋማትን የሚመሰርቱ ህጎች በፖሊሲው መካተታቸውን ጠቁመዋል።
የእነዚህ ተቋማት መመስረት በማህበረሰቡ ዘንድ ተዓማኒነት ያላቸው ተቋማት አስፈላጊ መሆናቸውን ጠቁመው፥ ለተጎጂዎች ትኩረት የሰጠ አካታች ሂደትን የተከተለ የተቋማት ምስረታ አስፈላጊ ስለመሆኑም ገልጸዋል።
በቀጣዮቹ ሶስት ወራት የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ማስተግበሪያ አዋጆች ጸድቀው ወደ ስራ እንዲገቡ ለማስቻል እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አበባ እምቢያለ፤ የኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ግልፅ በሆነ መንገድ መዘጋጀቱን ጠቅሰው፥ መድረኩ የሽግግር ፍትህ ዓላማዎችን ለማሳካት የተነደፈ መሆኑንም ተናግረዋል።
በፖሊሲው የተገለጹትን ዓላማዎች በትክክል ለማስፈጸም አዳዲስ ሕጎች ሊወጡ እንደሚገባ ፖሊሲው የሚያመላክት መሆኑንም ገልጸዋል።
በመድረኩ ላይ የአህጉራዊው የደህንነት ጥናት ኢንስቲትዩት የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ዳይሬክተር ፖል-ሲሞን ሃንዲ እንዲሁም የዘርፉ ዓለም አቀፍ ባለሙያዎች ተገኝተዋል።