በድሬዳዋ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች የተመቻቸው የድጋፍ መረሃ ግብር ወደ ምርታማነት እያሸጋገረ ነው

ድሬዳዋ፤ታህሳስ 1/2017(ኢዜአ)፥ በድሬዳዋ አስተዳደር በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች የተመቻቸው የድጋፍ መረሃ ግብር ከተረጂነት እያላቀቀ ወደ ምርታማነት እያሸጋገረ መሆኑን የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ ተናገሩ።

በአለም ባንክና በመንግስት ድጋፍ
በከተሞች እየተተገበረ የሚገኘው የልማታዊ ሴፍትኔት መርሃግብር በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙትን የማህበረሰብ ክፍሎችን ህይወት እያሻሻለ ነው ብለዋል።

ተጠቃሚዎች በሚቆጥቡት ሀብትና ለስራ በሚሰጣቸው የስራ መነሻ ተንቀሳቅሰው ከተረጂነት ወደ ምርታማነት በሚያሸጋግሩ ስራዎች እየተሰማሩ የምግብ ዋስትናቸውን እያረጋገጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

እንደ አቶ ሀርቢ ገለፃ፤ ዘንድሮ በሚጀመረው አዲስ መርሃግብር ተጠቃሚ የሚሆኑትን በተገቢው መንገድ በመለየት፣ የተቀናጀ ድጋፍና ክትትል በማድረግ የተሻለ ለውጥ እንዲመጣ መትጋት ይገባል።

ባለፉት ሶስት ዓመታት በመርሃግብሩ ተጠቃሚ ከሆኑት 7ሺህ 440 በላይ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ከሚገኙ ሰዎች መካከል ከ6ሺህ 250 በላይ የሚሆኑት ወደ ዘላቂ የኑሮ ማሻሻያ የልማት ስራዎች የሚሰማሩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ዘንድሮ በሚጀምረው መርሃ ግብር ከ9ሺ በላይ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ሰዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ የምልመላው ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም