ቀጥታ፡

በአፋር ክልል እየተሰጠ ያለው የሥራ ዕድል ፈጠራ ስልጠና የተፈጥሮ ፀጋዎችን አልምቶ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ የሚያግዝ ነው - ኢንስቲትዩቱ

ሠመራ፤ ታህሳስ 1/2017(ኢዜአ)፦ በአፋር ክልል በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ የሚሰጠው ስልጠና የክልሉን የተፈጥሮ ፀጋዎች አልምቶ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ በር እንደሚከፍት የኢትዮጵያ ኢንተርፕርነሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት ገለጸ።

ኢንስቲትዩቱ ከሰመራ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በኢንተርፕርነርሽፕ እና በንግድ ሥራ ክህሎት ላይ የአሰልጣኞች ስልጠና መስጠት ጀምሯል።


 

ከኢንስቲትዩቱ ስልጠናውን እየሰጡ ያሉት አቶ ወልደማርያም ልሳኑ ስልጠናው በአፋር ክልል ያሉ የተፈጥሮ ጸጋዎችን በማልማት ለሥራ ዕድል ፈጠራ ለማዋል ሚናው የጎላ መሆኑን ገልፀዋል።

ስልጠናው የክልሉን የተፈጥሮ ፀጋዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማልማትና ለሥራ ዕድል ፈጠራ ለማዋል ያለመ መሆኑንም አመልክተዋል።

በአሰልጣኞች ስልጠና ላይ የዩኒቨርሲቲው መምህራን እየተሳተፉ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ በቀጣይም ተግባር ተኮር ስልጠናውን ለበርካታ ሥራ ፈጣሪዎች ተደራሽ ለማድረግ ታቅዷል ብለዋል።


 

በስልጠናው ላይ የተገኙት የሠመራ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ዓሊ በበኩላቸው እንደገለጹት የአስልጣኞች ስልጠና መዘጋጀቱ ለበርካታ የአፋር ክልል ወጣቶች የሥራ እድል ፈጠራን ለማስፋት የሚያስችል ነው።

በቀጣይ ከክልሉ ስራና ክህሎት ቢሮ ጋር በመተባበር ሥራ አጥ ወጣቶችን ለይቶ ስልጠናዎችን በስፋት መሥጠት እንደሚያስችልም አቶ አደም ተናግረዋል።

የወጣቶችን አቅምና ፍላጎት መሰረት በማድረግ ቀጣይነት ባለው መልኩ ስልጠናው እንደሚሰጥም ገልፀዋል።

ከዚህ ቀደም ለ90 የሠመራ ዩኒቨርሲቲ መምህራን በኢንተርፕነርሽፕ፣ በንግድና በሥራ ክህሎት ተግባር ተኮር ያልሆነ ስልጠና ከወሰዱት መካከል የተሻለ አፈጻጸም ያስመዘገቡ 40ዎቹ የአሁኑን ተግባር ተኮር ስልጠና እየወሰዱ መሆኑን አስረድተዋል።

ዛሬ የተጀመረው የአሰልጣኞች ስልጠና ተግባር ተኮር ሲሆን ለአንድ ሳምንት ይቆያል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም