ቀጥታ፡

የአዋጁ ማሻሻያ የኢትዮጵያን ዕድገት ታሳቢ ያደረገ የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድን ማዘመን የሚያስችል ነው - ተስፋዬ ቤልጅጌ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 1/2017(ኢዜአ)፦ የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ዕድገት ታሳቢ ያደረገ የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድን ለማዘመንና የህግ ተጠያቂነትን ማረጋገጥ የሚያስችል መሆኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ(ዶ/ር) ገለጹ።


 

የህዝብ ተወካዮች ምክ ቤት በ10ኛ መደበኛ ስብሰባው የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ አዋጅ የማሻሻያ ረቂቅ ላይ ተወያይቶ ለውሃ መስናኖ ቆላማ አካባቢ እንዲሁም ለከተማ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች መርቷል።

የአዋጁን ማሻሻያ አስመልክቶ ለምክር ቤቱ ማብራሪያ የሰጡት በምክር ቤቱ የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትሩ ተስፋዬ ቤልጅጌ(ዶ/ር) ከኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገትና ከህዝብ ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ የሚመነጨው የቆሻሻ መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሆኑን ገልጸዋል።

ከከተሞች ፈጣን ዕድገት ጋር ተያይዞ የሚመነጨው ቆሻሻ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ካልተያዘና ካልተወገደ በህብረተሰቡ ጤና፣ በምርታማነት እና በአካባቢ ደህንነት ላይ አሉታዊ ተፅእኖ ያስከትላል ብለዋል።

ከዚህ ባለፈ ለገፀ ምድርና የከርሰ ምድር ውሃ ብክለት፣ ለተለያዩ የጤና ጠንቅ የሆኑ ተዋህስያን መፈጠር መንስኤ መሆኑን አንስተዋል።

ከተሞች ማራኪ፣ ጽዱና ውብ እንዳይሆኑ ምክንያት የሆነው የደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ላይ ያሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታት የአዋጁ መሻሻል ሚናው የጎላ ነው ብለዋል።

ላለፉት 13 ዓመታት ሲተገበር በቆየው የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ አዋጅ ቁጥር 513/1999 በደረቅ ቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ላይ የሚታዩ ችግሮችን መፍታት አለመቻሉን አብራርተዋል።

በመሆኑም የህግ ተጠያቂነትን የሚያሰፍን የተሟላ የህግ ማዕቀፍ አሻሽሎ ማዘጋጀት አስፈላጊ በመሆኑ አዋጁ እንዲሻሻል መደረጉን አንስተዋል።

የማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ በአደገኛ ቆሻሻ ስር በሚመደቡ እንደ ኤሌክትሮኒክስና ኤሌክትሪክ ቆሻሻ አወጋገድ ላይ ተፈጻሚ አይሆንም።


 

የምክር ቤቱ አባላት በበኩላቸው የተሻሻለው ረቂቅ አዋጅ በተለይም የፕላስቲክ ውጤቶች እያሳደሩ ያሉትን አሉታዊ ተጽዕኖ መከላከል የሚያስችል መሆኑን አንስተዋል።

ረቂቅ አዋጁ የተመራለት ቋሚ ኮሚቴም የአዋጁን ዝርዝር ጉዳዮችና መካተት ያለባቸውን ድንጋጌዎች በትኩረት ማየት አለበት ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም