ቀጥታ፡

ኤግዚቢሽኑ በአቪዬሽን ዘርፍ የተሰማሩ ኩባንያዎች ልምድ በመቅሰም ተጨማሪ አቅም የሚፈጥሩበት ነው - ተሳታፊዎች

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 1/2017(ኢዜአ)፦ የሲቪል አቪዬሽን ኤግዚቢሽን በዘርፉ የተሰማሩ ኩባንያዎችና ቴክኖሎጂ ፈጣሪዎች ልምድ በመቅሰም ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር መሆኑን የቴክኖሎጂ ፈጠራቸውን ለዕይታ ያቀረቡ ተሳታፊዎች ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን የተመሰረተበትና የዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ማቋቋሚያ ስምምነት የተፈረመበት 80ኛ ዓመት በዓል በአዲስ አበባ እየተከበረ ነው፡፡

በስካይ ላይት ሆቴል በተዘጋጀው ኤግዚቢሽን ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎችና ድርጅቶችም የአቪዬሽን ዘርፍ ፈጠራቸውን ይዘው ቀርበዋል፡፡


 

በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ የኤሮስፔስ ተመራማሪ ኢንጂነር ገዛኸኝ ረታ፤ በዩኒቨርሲቲው በሙከራ ደረጃ በተሳካ ሁኔታ ያስወነጨፉትን የሶሊድ ታይፕ ሮኬት ለእይታ አቅርበዋል፡፡

ምርምሩ የኢትዮጵያን የሕዋ ሳይንስ ዘርፍ የሚያግዝ መሆኑን ገልጸው፤ ኤግዚቢሽኑ በዘርፉ የተሰማሩ ግለሰቦችና ኩባንያዎች ልምድ በመውሰድ አቅማቸውን የሚያሳድጉበትን እድል ይፈጥራል ብለዋል፡፡


 

በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኮምፒውተር ኢንጂነሪንግ መምህር የሱፍ ጀማል በበኩላቸው በኤግዚቢሽኑ ያቀረቡት የአቪዬሽን ዘርፍ የተግባቦት መቆጣጠሪያ ስርዓት ሀገር በቀል እውቀትን በመጠቀም በራሳቸው አቅም ያመረቱት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ይኸውም ከውጭ የሚገባውን ቴክኖሎጂ ከማስቀረት ባለፈ ድሮኖችን፣ ሰው አልባ ተሽከርካሪዎችን እና የጦር መሳሪያዎችን ከሰው ንክኪ ውጭ መገልግል የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል፡፡


 

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ዋና ስራ አስፈፃሚ ጌታቸው መንግስቴ፤ ዓለም አቀፍ ሲቪል አቪዬሽንን ከመሰረቱት ሶስት የአፍሪካ ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ መሆኗን ጠቅሰዋል፡፡

ኢትዮጵያ የአቪዬሽን ዘርፉን በተቀላቀለች አጭር ጊዜ ውስጥ ተጨባጭ ለውጥ ማስመዝገቧን ገልጸው፤ ወቅቱን የሚመጥን አቅም ለመገንባት በሰው ሀብት ልማት ላይ በትኩረት እንሰራለን ብለዋል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ የአየር ትራንስፖርት ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱን ገልፀው፤ ኢትዮጵያ ዘመኑንና ታሪኳን የሚመጥን የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ለመገንባት እንቅስቃሴ መጀመሯን ተናገርዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም