ቀጥታ፡

መንግስት ለስታርት አፕ የሰጠው ህጋዊና ተቋማዊ ትኩረት ለዘላቂ እድገት መሰረት የሚጥል ነው-በዘርፉ የተሰማሩ ወጣቶች

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 1/2017(ኢዜአ)፦መንግስት ለስታርት አፕ የሰጠው ህጋዊና ተቋማዊ ትኩረት ለዘላቂ እድገት መሰረት የሚጥል መሆኑን በዘርፉ የተሰማሩ ወጣቶች ተናገሩ።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በበኩሉ በኢትዮጵያ ምጣኔ ሃብት ውሰጥ የግሉን ዘርፍ ሚና ለማሳደግ ለስታርት አፕ ህጋዊ ማዕቀፍና ከለላ ትኩረት መስጠቱን ገልጿል።

የስታርት አፕ ማህበራት ኃላፊዎች ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ዘርፉ ተቋማዊና ህጋዊ ትኩረት ማግኘቱ ለስራቸው ዘላቂ እድገት ጉልህ ድርሻ እንዳለው አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ስራ ፈጣሪ ወጣቶች ማህበር ፕሬዝዳንት ሳሚያ አብዱል ቃድር መንግሥት ቀደም ሲል ለዘርፉ ተገቢውን ትኩረት ባለመሰጠቱ ወደ ዘርፉ ለመግባት አበረታች ሁኔታዎች እንዳልነበሩ አስታውሳለች።

አሁን ላይ መንግሥት ለጥያቄዎቻቸው ምላሽ በመስጠት ለስታርት አፕ የሰጠው ትኩረት የወጣቱን ስራ ፈጣሪነት እንደሚያበረታታ ገልጻለች።

ስታርት አፕ ፈጠራና ቴክኖሎጂን መሰረት በማድረግ በቀላሉ ተደራሽ፣ ችግር ፈቺና በተለያዩ ዘርፎች እሴት መጨመር የሚችል በመሆኑ “እንደ አገር ትልቅ የምጣኔ ሃብት ግብአት ነው” ብላለች።

እንደ ሀገር ስታርትአፕ በአዋጅ ደረጃ ህጋዊና ተቋማዊ ትኩረት ማግኘቱ ውጤታማ ለመሆንና ለዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት እንደሆነ ወጣት ሳሚያ ተናግራለች።


 

በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የኢኖቬሽንና ስታርት አፕ ልማት መሪ ስራ አስፈጻሚ ሰላምይሁን አደፍርስ በበኩላቸው የዘርፉን ዘላቂ እድገት ለማረጋገጥ ለህጋዊ ማዕቀፍ ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል።

ፈጠራን ከምጣኔ ሃብት እድገት ችግሮች፣ ከዓለም ነባራዊ ሁኔታና ሌሎች የአገሪቱ ህግና ፖሊሲዎች ጋር በማናበብ ለምጣኔ ሃብትና ለማህበራዊ ልማት ጥቅም ላይ ለማዋል እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

በዓለም ግዙፍ ምጣኔ ሃብት በፈጠሩ አገሮች ስታርት አፕ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ገልጸው ይህንኑ በኢትዮጵያም ለመቃኘት እየተሰራ ነው።


 

የኢትዮጵያ ስታርት አፕ ኢኮ ሲስተም ማህበር ፕሬዝዳንት ብሩክ ዮሴፍ በበኩሉ የስታርት አፕ ዘርፍን ምህዳር ምቹ ለማድረግ ሲያነሷቸው የነበሩ ጥያቄዎች ምላሽ እያገኙ መሆኑን ተናግሯል።

ምህዳሩን ምቹ ለማድረግ በአዋጅ የተቀመጡ አሰራሮች በተግባር ውጤታማ እንዲሆኑ ከመንግስት ጋር በትብብር እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

ወጣቶች እንዲሁም ሌሎች በስታርት አፕ ዘርፍ የተሰማሩ የተፈጠረውን እድል በመጠቀም ለውጤታማነት መትጋት እንደሚገባቸው የማህበራቱ ኃላፊዎች አስገንዝበዋል።

ስታርት አፕ ለውጦችን ሊያመጣ የሚችል በሙከራ ላይ ያለ የንግድ ሃሳብ ሲሆን በተለይም ደግሞ በቴክኖሎጂ የተደገፉ አሰራሮች ላይ መሰረት ያደረገ ነው። 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም