የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ምሰሶ የሆነው ግብርና እመርታ እያሳየ ነው - ግርማ አመንቴ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ምሰሶ የሆነው ግብርና እመርታ እያሳየ ነው - ግርማ አመንቴ(ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 1/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ምሰሶ የሆነው ግብርና እመርታ እያሳየ ነው ሲሉ ግርማ አመንቴ(ዶ/ር) ገለጹ።
ሚኒስትሩ ከታንዛኒያን ልዑካን ቡድን ጋር በአሁናዊ የኢትዮጵያ ግብርና ቁመና ዙሪያ ተወያይተዋል።
በውይይቱ ላይም ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ባስመዘገበቻቸው ስኬቶች ዙሪያ ሚኒስትሩ ለታንዛኒያ ልዑካን ቡድን ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በማሳደግ ረገድ ለተለዩ ቁልፍ ተቋማት (ግብርና፣ ማዕድን፣ ቱሪዝም፣ ኢንዱስትሪና አይሲቲ) ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑንም ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ግብርና ለሀገሪቱ 1/3ኛ አጠቃላይ ዕድገት፣ 2/3ኛ ኤክስፖርት እንዲሁም 65 በመቶ የሥራ ዕድል ምንጭ መሆኑን አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ምሰሶ የሆነው ግብርና እመርታ እያሳየ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፣ የአጋር አካላትንና የፕሮጀክቶችን ድጋፍ ከግብርና ሚኒስቴር ጋር አንድ ዕቅድና አንድ ሪፖርት እንዲኖራቸው እየተደረገ ነው ሲሉ ገልፀዋል፡፡
ከገጠሩ ክፍል ባሻገር የከተማ ግብርና ከፍተኛ ለውጥ እያመጣ መሆኑንም ዶክተር ግርማ ጠቁመዋል፡፡
የሕብረተሰቡን የእንስሳት ተዋጽኦ ፍላጎት ለማሟላት ብሔራዊ ኢኒሼቲቭ ተቀርጾ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው የወተት፣ ዶሮ፣ ማር እና ዓሳ መንደሮችን በየአካባቢው በመመስረት ውጤታማ መሆን ችለናል ብለዋል፡፡
እነዚህን መንደሮች ማስፋፋት ከውጭ የሚገባውን የዶሮ ስጋ ለማስቀረት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የልዑካን ቡድኑ አባላት ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ እያስመዘገበች ያለውን ለውጥ አድንቀው የሁለትዮሽ ትብብሩ አንዱ ከሌላው ልምድ እንዲቀስም የሚያስችል መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የታንዛኒያ ልዑካን ቡድን አባላት በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ የልምድ ልውውጥ የሚያደርጉ ሲሆን በእንስሳት ልማቱ የተገኙ ተሞክሮዎችንም እንደሚጎበኙ ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።