በአገራዊ ምክክሩ የኦሮሚያ ክልልን ወክለው የሚሳተፉ አካላትን ለመምረጥ አመቻቾች ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸው ተመለከተ - ኢዜአ አማርኛ
በአገራዊ ምክክሩ የኦሮሚያ ክልልን ወክለው የሚሳተፉ አካላትን ለመምረጥ አመቻቾች ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸው ተመለከተ
አዳማ ፤ ታህሳስ 1/2017(ኢዜአ)፡- በአገር ደረጃ በሚካሄደው ምክክር የኦሮሚያ ክልልን ወክለው የሚሳተፉ አካላትን ለመምረጥ የሚደረገውን ሂደት ውጤታማ ለማድረግ አመቻቾች ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸው ተመለከተ።
የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን በኦሮሚያ ክልል ከታህሳስ 7/2017 ዓ.ም ጀምሮ ለሚካሄደው የአጀንዳ አሰባሰብና የምክክሩ ተሳታፊ አካላት መረጣን እንዲያመቻቹ ለተመለመሉ አመቻቾች በአዳማ ስልጠና መስጠት ተጀምሯል ።
በኮሚሽኑ የኦሮሚያ ክልል ምክክር ሂደት አስተባባሪ አቶ ብዙነህ አሰፋ ፤ ስልጠናው በክልሉ አጀንዳ የሚሰጡና ማህበረሰቡን ወክለው የሚሳተፉ አካላትን እንዲመርጡ ለማስቻል ነው ብለዋል።
በአገራዊ ምክክሩ የሚሳተፉትን ለመምረጥ ሁኔታዎችን የሚያመቻቹ አካላት ሚና ቁልፍ መሆኑን ጠቅሰው፤ እነዚህም በክልሉ ከሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ባላቸው የዕውቀት፣ክህሎትና ትምህርት ብቃት የተመረጡ ናቸው ሲሉ ገልጸዋል።
አመቻቾቹ ከዚህን በፊት የኮሚሽኑ ተባባሪ አካላት መረጣ ላይ አጋዥ ስራ ማከናወናቸውን አውስተው፤ በተለይ አጀንዳ የማሰባሰብ ስራ የተሳካ እንዲሆን፣ የምክክሩ ተሳታፊዎች መረጣ ላይ የዕውቀትና ሙያዊ ድጋፍ እንዲሰጡ የተመረጡ እንደሆኑ አመልክተዋል።
ስልጠናው የህዝቡን ዘላቂ ጥቅም ማስጠበቅ የሚችሉ አጀንዳዎች እንዲሰበሰቡና እንዲሰጡ ለማስቻል መሆኑን ገልጸዋል።
ይህም አርሶና አርብቶ አደሮች፣ ሴቶች ፣ ወጣቶች ፣ ምሁራን፣ የመንግሥት ሰራተኞች፣ አካል ጉዳተኞች ፣ የማህበረሰብ መሪዎች አጀንዳ የመስጠት ተግባር ላይ እንዲሳተፉ ማስቻል ነው ብለዋል።
በዚህም በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ በህዝብ የተሰጣቸውን ውክልና በአግባቡ በመወጣት ወካይ አጀንዳ ማቅረብ እንዳለባቸው አመልክተዋል።
በኮሚሽኑ የአጀንዳ ቀረፃና ምክክር አስተባባሪ አቶ ተመስገን አብዲሳ በበኩላቸው፤ የአጀንዳ አሰባሰብ ሂደቱን የተሳካ ለማድረግ የክልሉን ቋንቋ በተገቢው መረዳትና ማስረዳት የሚችሉ ምሁራን ተለይተው በአመቻችነት እየሰለጠኑ ናቸው ብለዋል።
የአጀንዳ መሰብሰብ ሂደትን በቅንጅት የማመቻቸት ስራ የሚያከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በአጀንዳዎች አቀራረብ ዙሪያ ሊኖሩ የሚችሉ ክፍተቶችን ለመሙላት የቅሬታ ሰሚ ቡድን ተደራጅቶ እየሰራ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።
ባለፉት ጊዜያት የኮሚሽኑን ዓላማና ተልዕኮ ለህዝብ የማስገንዘብና የአጀንዳ ልየታ ስራዎች በአብዛኛው ክልሎችና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች አከናውኗል።
በተጨማሪም የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱን በሶማሌ፣ በጋምቤላ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በአፋር፣ በደቡብ ኢትዮጵያ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች እንዲሁም በአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች መከናወኑንም ቀደም ብሎ ተገልጿል።